ዘላቂ ሰላምንና የህዝቦችን ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳ ነው- አቶ ርስቱ ይርዳው

82

ሐዋሳ ሐምሌ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል መንግስት በቀጣይ በጀት ዓመት ዘላቂ ሰላምና የህዝቦች ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ እየተወያየ ነው።

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የቀጣዪን በጀት ዓመት እቅድ ሲያቀርቡ እንደገለጹት ሰላምን ማስፈንና የህዝቦችን ደህንነት በማረጋጥ የሃገርን ሉአላዊነት መጠበቅ ቀዳሚ የክልሉ መንግስት አጀንዳ ነው ብለዋል።

ለብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ውጤታማነት መስራት የህግ የበላይነት ማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይም ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚነሱ የተለያዩ የመዋቅር ጥያቄዎች በሰላማዊና ህጉን መሰረት ባደረገ መልኩ ከህዝቡ ጋር በውይይት ለመፍታት የተጀመረው ስራ ቀጣይነት እንደሚኖረውና ጥያቄው ምላሽ እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ ግጭቶችን መፍታትና ዘላቂ ሰላምን በማሰፈን ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በግብአት አቅርቦት፤ የቴክኖሎጂና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን በማስፋፋት የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በስፋት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

በአረንጓዴ ልማት ስራ፤ በወጣቶችና ሴቶች ዘርፍና በሌሎችም ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችና ግቦች ላይ የተቀመጠውን እቅድ አቅርበዋል።

የምክር ቤት አባላትም በቀረበው የእቅድ ሪፖርት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች እያቀረቡ ነው።

ጉባኤው በክልሉ በ2015 ረቂቅ የበጀት አዋጅና በቀሪ አጀንዳዎች ላይ የሚወያይ ሲሆን የተለያዪ ሹመቶችንም እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም