ቦትስዋና፣ዩጋንዳ እና ጋና በሴት የስራ ፈጣሪዎች ብዛት ከአለም ግንባር ቀደም ሀገራት ሆኑ

499

ሐምሌ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ቦትስዋና፣ዩጋንዳ እና ጋና ሴት የስራ ፈጣሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በኢኮኖሚው ውስጥ በማሳተፍ ከአለም ሀገራት ግንባር ቀደም እንደሆኑ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን አመለከተ።

ፋውንዴሽኑ እ.አ.አ በ2021 ባወጣው መረጃ መሰረት ቦትስዋና 38 ነጥብ 5 በመቶ፣ ዩጋንዳ 38 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም ጋና 37 ነጥብ 2 በመቶ ሴት የስራ ፈጣሪዎችን ለሶስት ተከታታይ አመታት በኢኮኖሚው ውስጥ በማሳተፍ ከአለም ሀገራት ግንባር ቀደም ናቸው።

ሪፖርቱ ከቦትስዋና፣ዩጋንዳ እና ጋና በተጨማሪ ናይጄሪያ እና አንጎላ ከአፍሪካ በርካታ ሴት የስራ ፈጣሪዎች የሚገኙባቸው ሀገራት እንደሆኑ አመላክቷል።

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ሴት የስራ ፈጣሪዎች ሪፓርት ለአምስተኛ ግዜ የተዘጋጀ ሲሆን በአለም ዙሪያ የሴቶችን የስራ ፈጣሪነት የሚያበረታታ እንዲሁም ሴቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያሳይ ነው።

ሪፖርቱ በተለይ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በስራ ፈጠራ ውስጥ ያሉ ሴቶች ምቹ የሆነ የስራ አካባቢን ካለማግኘት ጀምሮ በፋይናንስ አቅርቦት እጥረት፣የተሻለ የትምህርት እድልን በማጣት እንዲሁም በመዋቅራዊ ችግሮች እንደሚፈተኑ አሳይቷል።

በአፍሪካ በተለይ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኙ ሴት የስራ ፈጣሪዎች ከወንዶች በተሻለ ሁኔታ ለስራ ፈጠራ የሚተጉ እና የተለያዩ ሙከራዎችን የሚያደርጉ እንደሆኑም ሪፓርቱ አስነብቧል።

በማስተርካርድ ፋውንዴሽን የምእራብ አፍሪካ ሀገራት የቢዝነስ አካባቢ ሀላፊ የሆኑት ኤቤሂጄ ሞሞህ እንዳሉት በቦትስዋና፣ዩጋንዳ፣ጋና፣ናይጄሪያ እና አንጎላ የሚገኙ ሴት የስራ ፈጣሪዎች ለአለም እና ለተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ መሆን የሚችሉ ጠንካራ የስራ ፈጠሪዎች ናቸው።

በነዚህ ሀገራት የሚገኙ ሴቶች ከፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ምቹ ያልሆኑ ህግ እና ደንቦች እንዲሁም የቴክኒክ ችግሮችን ተቋቁመው በኢኮኖሚው ውስጥ ጎልተው ወተዋል ብለዋል።

ማስተርካርድ ሴቶች በስራ ፈጠራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ በአለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ2025 በአጠቃላይ 25 ሚሊዮን ሴት የስራ ፈጣሪዎችን ከዲጂታል ኢኮኖሚው ጋር ለማገናኘት እየሰራ ይገኛል ሲል የዘገበው ቢዝነስ ኢንሳይድ አፍሪካ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም