በአንጋፋው አርቲስት አሊ ቢራ ስም በድሬዳዋ ከተማ ፓርክ ተሰየመ

110

ሐምሌ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ)አንጋፋው አርቲስት አሊ ቢራ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘው ፓርክ በስሙ ተሰይሟል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለከተማዋ እድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ለተባሉ ግለሰቦች በስማቸው ቦታ ሰይሞላቸዋል።

በተጨማሪም አስተዳደሩ እድሳት የተደረገላቸውን የሚሊኒየም መናፈሻ ፓርክና ድልድይ ዛሬ አስመርቋል።

አንጋፋው አርቲስት አሊ ቢራ በከተማዋ የሚገኘው የሚሊኒየም መናፈሻ ፓርክ “አሊ ቢራ ፓርክ” በሚል እንዲሰየም ተደርጓል።

ከአርቲስቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ድሬዳዋን የመሩት ከንቲባ አልፍሬድ ሻፊ ድሬደዋን በመሩበት ወቅት ያሰሩት ድልድይ ታድሶ በስማቸው እንዲሰየም ማድረጉን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አሊ ቢራ ለሕዝብ ነጻነት እና እኩልነት ትግል ማድረጉን እና ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎችን ማበርከቱን ገልጸዋል።

የቀድሞው የድሬዳዋ ከንቲባ አልፍሬድ ሻፊ በመሪነት ዘመናቸው ሕዝቡን ከጎን በማሰለፍ በአርያነት የሚጠቀስ ማህበራዊና የምጣኔ ሃብት እንዲመዘገብ የጎላ አስተጽኦ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ታላቅ ውለታ የፈጸሙ ጀግኖችን መዘከርና ማስታወስ ብሎም በስማቸው ቅርስ ማኖር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የድሬዳዋ ታሪካዊ ሁነቶች፣ቅርሶችና የሕዝብ እሴቶች የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነቷን እንደሚያሳድጉት ገልጸዋል።

"ናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት" መርሃ ግብር ከሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም