ብልፅግና ፓርቲ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በቀጣናው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከቀንዱ አገራት አቻ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት ይሰራል

77

ሐምሌ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ብልፅግና ፓርቲ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በቀጣናው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከቀንዱ አገራት አቻ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

በሰላምና መረጋጋት እጦት የሚፈተነው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በረሃማነት መስፋፋት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ አንበጣ፣ ሰደድ እሳትና መሰል ተፈጥሯዊ ችግሮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነውበታል።

በዚህም በቀጣናው በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ ችግሮች በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሀብና መፈናቀል እየዳረጉት ይገኛሉ፡፡

ከዚህ አኳያ በቀጣናው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ሁለንተናዊ ቀውሶችን ለመግታት ተናጠላዊ ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ የፖሊሲ መፍትሔ እንደሚሻ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ የምትሰኘው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ ስትራቴጂ ቀርጻ ገቢራዊ እያደረገች ቢሆንም ከጎረቤት አገራት ጋር በቅንጅት ካልሰራች የሌሎች ዳፋ ለእርሷም መትረፉ አይቀሬ ነው።

የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ኢትዮጵያ የምታከናውነው አረንጓዴ ልማት ብቻውን ቀጣናው ለተጋረጠበት ፈተና ምላሽ እንደማይሆን ያምናሉ።

በዚህም ፓርቲው ከየአገራቱ አቻ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጎረቤት አገራት እንዲጋሩት የማድረግ ሥራ ባለፈው ዓመት መጀመሩን አስታውሰዋል።

ፓርቲው በቀጣይም በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ከቀጣናው አገራት አቻ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በፓርቲው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ችግር በአንድ አገር ሳይወሰን ሁሉንም ተጋላጭ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ለቀጣይ ትውልድ የለመለመች ኢትዮጵያን ለማውረስ መንግሥት እየሰራ ቢሆንም የኢትዮጵያ ጥረት ብቻ ለቀጣናው መልከ-ብዙ ችግሮች መፍትሔ እንደማይሆን ገልጸዋል።

በዚህም ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያና በዙሪያዋ ያሉ የቀንዱ አገራት በአረንጓዴ ልማት ላይ በቅንጅት እንዲሰሩ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም