ኢራንና ሩስያ የ40 ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ሀብት ልማት ስምምነት ተፈራረሙ

606

ሐምሌ 13 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢራን ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያና የሩስያው ነዳጅ አቅራቢ ጋዝ ፕሮም የ40 ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ሀብት ልማት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በበይነ መረብ ትናንት በተካሄደው የፊርማ ስነ ስርዓት የኢራኑ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሞህሴን ኮጃስቴህ ሜር እና የጋዝ ፕሮም የአስተዳደር ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር ቪታሊ ማርኬሎቭ ተሳትፈዋል።

ስምምነቱ የተፈረመው የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኢራን አቻቸው ኢብራሂም ራይሲ እና ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲጵ ታይብ ኤርዶሃን ጋር ለመምከር ቴህራን ባቀኑበት ወቅት ነው።

ስምምነቱ የተለያዩ የነዳጅና የጋዝ ፕሮጀክቶች ልማት እንደሚያካትት የኢራኑ የዜና ወኪል ሻና ዘገባ ያመለክታል።

ጋዝ ፕሮም ” ኖርዝ ፓርስና ሰሜናዊ ኪሽ’ ለተሰኙት የጋዝ ማምረቻ ቦታዎች ልማት የኢራን ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ እንደሚደግፍ ተገልጿል።ተጨማሪ ስድስት የጋዝ ማምረቻ ቦታዎችን እንዲለሙ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።

ስምምነቱ ኩባንያዎቹ እርስ በእርሳቸው የጋዝና የጋዝ ምርቶችን መሸጥና መለዋወጥ፣ በግንባታ ላይ ያሉ የተጣራ ነዳጅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲጠናቀቁ ማድረግን ያከትታል።

ወደ ውጪ አገር ለሚልኩት ጋዝ የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ማካሄድ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።

“ታሪካዊ” በተባለው ስምምነት “በኢራን የነዳጅ ኢንዱስትሪ ታሪክ ትልቅ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስተመንቶች መካከል አንዱ ነው” ሲሉ የኢራን ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሞህሴን ኮጃስቴህ ሜር ገልጸዋል።

ኢራንና ሩስያ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት ካላቸው 10 አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም