በኢትዮጵያ የህንድ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት መጠን 5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል

140

ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የህንድ ባለለሀበቶች የሚያፈሱት የማዋዕለ ነዋይ መጠን 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በህንድ ኒው ዴህሊ በተካሄደው 17ኛ ህንድ -አፍሪካ የንግድ ትብብር ስብሰባ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ነው።

ሚኒስትሩ እንዳሉት በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለው የንግድ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት እድገትን እያሳየ የመጣ ሲሆን የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት 650 የህንድ ኩባንያዎች በኢትየጵያ ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛሉ፤ ይህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የውጭ ሀገራት ኢንቨስትመንት ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ አድረጓቸዋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ኩባንያዎቹም በአጠቃላይ ከ75 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር ከውጭ ኩባንያዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም መንግስት በግሉ ዘርፍ የሚመራ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመፍጠር እያደረገ የሚገኘውን ማሻሻያዎች አብራርተዋል።

መንግሰት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እና የአስር አመት የልማት እቅድን እየተገበረ ይገኛል፤ ይህም ማክሮ ኢኮኖሚውን በማሻሻል የውጭ ምንዛሬ አለመመጣጠንን ለማስተካከል፣የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሻሻል እና የብድር ዘላቂነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ማማ እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ኢትዮጵያ የቀጠናው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሏትን የዘርፍ ማሻሻያዎችን እንዲሁም ምቹ ደንቦችንና መሰረተልማቶችን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባወን ምርት ለማስቀረት በኬሚካል፣ በመድሃኒት ማምረቻ ፣ኮንስትራክሽን እና ምህንድስና ዘርፍ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ፣ የጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣የግብርና መቀነባበሪያ ለመሳሰሉት የማኑፋክቸሪን ዘርፎች ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰሩ 22 የኢንደስትሪ ፓርኮች እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ሚኒስትሩ ህንድ በአፍሪካ የተሰባጠረ እና ቅንጅት ያለው ኢኮኖሚ ለምፍጠር ያሳየቸውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

የህንድ-አፍሪካ ትብብር ስብሰባ በየአመቱ የሚካሄድ ሲሆን በህንድ የኢንዱስትሪዎች ኮንፌዴሬሽ እና የህንዱ እግዚም ባንክ ከህንድ የውጭ ጉዳይ እንዲሁም የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስትሮች ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ነው።

ስብሰባው በአፍሪካ እና በህንድ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት በማጠናከር የህንድ ድንበር ዘለል አጋርነት እንዲዳብር አላማውን ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም