የማጂና የቤሮ ነዋሪዎች የአስተዳደርና የልማት ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

580

ሚዛን መስከረም 4/2011 በቤንቺ ማጂ ዞን የማጂና የቤሮ ወረዳዎች ነዋሪዎች የአስተዳደር አደረጃጀትና የልማት ጥያቄያቸው መንግስት ፈጣን ምላሽ እንደሰጣቸው ዛሬ በማጂ ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ ጠየቁ፡፡

በሰልፉ ቀድሞ የነበረው የማጂ ዞን አደረጃጀት ወደ ነበረበት የመመለስ፣ ለዓመታት ሳይፈታ የዘለቀው የሰላምና የጸጥታ ችግር ምላሽ ይሰጠው፣ እንዲሁም የልማት ጥያቄያቸው ሊመለስ ይገባል የሚሉ ነዋሪዎቹ አንስተዋል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡት የሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታደመ ኮሞሮ እንዳሉት ማጂ ጥንታዊትና ታሪካዊ ከተማ ብትሆንም እስከ አሁን የመሰረተ ልማትና የጸጥታ ችግር አለተፈታላትም፡፡

በወረዳ ማዕከል እንኳን የመብራትና የውሃ መሰረተ ልማት አለመማላቱን ጠቁመው  መንግስት ችግረቸውን ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ማርቆስ ገብረስላሴ በበኩላቸው “የማጂና የቤሮ አካባቢ ነዋሪዎች ለበርካታ ችግሮች እንዲዳረጉ ያደረገው የመዋቅር አደረጃጀት ችግር ነው “ብለዋል፡፡

ከማጂ ወረዳ እስከ ዞን ማዕከል ከ210 ኪሎ ሜትር በላይ የሚርቅ መሆኑንና ይህም ህዝቡ ፈጠን አገልግሎት እንዳያገኝ በማድረግ ለከፍተኛ  ወጪና ለእንግልት እንደዳረገው አመልክተዋል፡፡

“የማጂና አካባቢው የቀድሞ መዋቅራዊ አደረጃጀት ወደ ነበረበት ሊመለስ ይገባልም “ብለዋል፡፡

አካባቢው የደቡብ ሱዳን ጠረፋማ አካባቢ በመሆኑ ለዓመታት የጸጥታ ችግር እንዳለበት ጠቁመው በዚህም  የሰው ህይወት እንደሚጠፋና  ንብረትም እንደሚዘረፍ ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት በአካባቢው አስተማኝና ዘላቂ ሰላም ሊያስፍን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የማጂ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አዲስምዕራፍ አለሙ በበኩላቸው ህዝቡ የሚያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች በአካባቢው እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

” አስተዳዳሩ  ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ምላሽ እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራም ይገኛል” ብለዋል፡፡

ህዝቡ ጥያቄውን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መግለጹ የሚበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡