በዓመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ላይ የሚታደሙ ምዕመናንን እና እንግዶችን ሰላም ለመጠበቅ ዝግጅት ተደርጓል

66

ሐምሌ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዓመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ላይ የሚታደሙ ምዕመናንን እና እንግዶችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጅት መደረጉን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ እንደገለጹት፤ የምዕመናኑንና የእንግዶችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅም የምስራቅ እና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የሐረሪ ክልል እና የፌዴራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቀናጅተው ዝግጅት አድርገዋል።
የንግስ በዓሉ ታዳሚዎች መጨናነቅ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ በተለይም የደብሩ መግቢያና መውጫ በሮች አካባቢ የኪስ ቦርሳቸውን፣ ሞባይላቸውን እና ሌሎች ንብረቶቻቸውን በጥንቃቄ እንዲይዙ አስገንዝበዋል።
እንዲሁም አሽከርካሪዎች ወደ ንግስ በዓሉ ሲመጡ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ መለያ ወይንም ከኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ በስተቀር ሌላ ለፖለቲካ ማራመጃ የሚሆን ዓርማና ምልክት ይዞ መገኘት የማይቻል መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ አሳስበዋል።
በንግስ በዓል ላይ ሶስት ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ እና የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪዎች ሲያዙ ውሳኔ ለመስጠት ዐቃቤ ህግና ጊዜያዊ ፍርድ ቤት መቋቋሙን ጠቁመው፤ የበዓሉ ታዳሚዎችም አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥማቸው በስልክ ቁጥር 0256665056 መጠቆም እንደሚችሉ አመላክተዋል።
የአካባቢው የመሬቱ አቀማመጥ ዳገታማ፣ ቁልቁለታማና ጠመዝማዛ በመሆኑ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግና ደንብ አክብረው በማሽከርከር ከአደጋ እንዲጠበቁ አሳስበው፤ ከሐምሌ 17 ቀን ጠዋት ጀምሮ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከጨለንቆ ከተማ እስከ ቀርሳ ከተማ ባለው ዋናው የተሸከርካሪ መንገድ ላይ ከባድ መኪና ማለፍ የተከለከለ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ላይ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት የሚመጡ በርካታ ምዕመናን፣ ቱሪስቶች፣ አምባሳደሮች እና ሌሎች እንግዶች በዞኑ ሜታ ወረዳ ቁልቢ ከተማ በሚከበረው ዓመታዊ የገብርዔል ንግስ በዓል ላይ ይታደማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም