የተፈጠረውን ለውጥ በመጠቀም የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ አሳድጋለሁ...የአማራ ክልል የቱሪዝም ቢሮ

69
ባህርዳር መስከረም 4/2011 በአገሪቱ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ የክልሉ መስህብ ስፍራዎች ከ12 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በሚበልጡ ቱሪስቶች እንዲጎበኙ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ። የቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም ለኢዜአ እንደገለጹት በባለፈው ዓመት በመጀመሪያዎቹ ወራት በክልሉ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የውጪ አገር ጎብኚዎች ቁጥር መቀመነስ አሳይቶ ነበር። ዘንድሮ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ወደ አገራቸው እየገቡ መሆናቸውን ጨምሮ የጎብኚዎችን ቁጥርም ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት 12 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሃገር ውስጥና 340 ሺህ 500 የውጪ አገር ጎብኚዎችን የመስህብ ሃብቶችን በማስጎብኘት ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን በላይ ብር ተሰብስቧል” ብለዋል። በዚህ ዓመት የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት በመጠቀምም 350 የውጪ አገር ጎብኝዎችንና 12 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማስጎብኘት ከሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማስገባት እየተሰራ ነው። “ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ ክልሉ እንደ ሀገር ሰላም የሰፈነበት መሆኑን ለአገር ውስጥና ለውጪ ጎብኝዎች በመገናኛ ብዙሃንና በበራሪ ወረቀቶች የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ነው” ብለዋል። እንዲሁም የመዳረሻ ስፍራዎችን በመንገድ መሰረተ ልማት ማስተሳሰር፣ በቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ፣ የመብራትና መሰል ልማቶችን ተደራሽ ማድረግና ላሎችም እንደሚከናወኑ አስረድተዋል። “በክልሉ ለቱሪዝም መዳረሻነት ከሚታወቁት የጣና ገዳማት፣የላሊበላ ውቅር አባያተ ክርስቲያናት፣የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትና የየሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በተጨማሪ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቅና የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው”ብለዋል። ከነዚህም መካከልም በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኘው አልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ አንበሳና ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳት መንጋ ያለበት መሆኑ ስለተረጋገጠ  አካባቢውን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው “በተጨማሪም ይስማንጉስ ወይም የውጫሌ ውል ስምምነት የተደረገበትን ቦታ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የልየታ ስራ ተከናውኗል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም