አቶ ኬት ቷዋች ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

96
ጋምቤላ መስከረም 4/2011 የቀድሞው የጋምቤላ  ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ኬት ቷዋች ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ። አቶ ኬት ቷች ከአባታቸው ከአቶ ቷዋች ቢተውና  ከእናታቸው ከወይዘሮ ኛዴኝ ዴንግ የካቲት 1958 ዓ.ም. በጅካዎ ወረዳ ቶንግዶል ቀበሌ ነበር የተወለዱት። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅካው አንደኛ ደረጃ ፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኢታንግ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በመቱ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለው አጠናቀዋል። የከፍተኛ ትምህርታቸውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት በዲፕሎማ የተመረቁ ሲሆን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ደግም በልማት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ወስደዋል። አቶ ኬት ቷዋች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በክልሉ ተለያዩ የስራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል ። ቀደም ሲል የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋህዴን/ ተብሎ ይጠራ የነበረውን የክልሉ መሪ ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር  እንደነበሩ ከህይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል። አቶ ኬት ቷዋች ከታህሳስ 1995 እስከ ነሐሴ 1997 ዓ.ም. የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ለክልሉ ልማትና እድገት መፋጠን በቅንነትና በታማኝነት እንዳገለገሉ ተመልክቷል። ከመንግስት መዋቅር ከወጡ በኋላም በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት  ከ2000 ዓ. ም  ጀምሮ ህይወታቸው እስከ አለፈበት ጊዜ ድረስ በባለሙያነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። አቶ ኬት ቷዋች በአደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ስርዓተ ቀብራቸው ዘመዶቻቸው፣ወዳጆቻቸውና  የስራ ጓዶቻው በተገኙበት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተፈጽሟል። አቶ ኬት ቷዋች ባለትዳርና የልጆች አባት ነበሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም