ወጣቱ መቻቻልና ልዩነትን የማክበር ባህል ማዳበር አለበት – የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት

1859

አዲስ አበባ መስከረም 4/2011 ወጣቱ የታገለለትን ለውጥ ከግብ እንዲደርስ የመቻቻልና ልዩነትን የማክበር ባህል ማዳበር እንደሚገባው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ እና የተባበረው ኦነግ (ኦሮሞ ነጻነት ግንባር) ፓርቲዎች አመራር አባላት አሳሰቡ።

በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች ላይ ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀል በተደረገ እንቅስቃሴ በወጣቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።

የተፈጠረውን ልዩነት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡት የፓርቲዎቹ አመራሮቹ “ወጣቶቹ የሚደግፉትን ፓርቲ ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ እንጂ የሌላውን አካል ፍላጎት መንካት ተገቢ አይደለም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተጀመረውን ብዝኃነት የሚያስተናግድ የዴሞክራሲያዊ ባህል አንዱ የሌላውን ሃሳብ፣ አርማና አመለካከት ማክበርና መቻቻል ሲሆን፤ ይህን ሥርዓት ማዳበር ካልተቻለ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚከብድ ገልጸዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዲማ ኖጎ እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት የነበረው የፖሊቲካ ባህል በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አይደለም። ይህም በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ለውጥ በወጣቶች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ማስተናገድ አልተቻለም።

በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ሂደት ለውጥ እንዲመጣ ግንባር ቀደም በመሆን ሲንቀሳቀስ የነበረው ወጣቱ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ዲማ፤ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል ወጣቱ የመቻቻል ባህልን ሊያዳብር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጠውታል።

የተባበረው ኦነግ አመራር ጄነራል  ኃይሉ ጎንፋ በበኩላቸው በሰለጠኑና ባደጉ አገራት ማንኛውም አሰተሳሰብ ያለው ሰው  የሌላውን በማይነካ መልኩ የራሱን መግለጽ ይችላል፣ በመሆኑም ወጣቶቻችን እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ሳይሉ መቻቻል አለባቸው ብለዋል

‘’ ወጣቶች ወይም ቄሮች ለረዥም ጊዜ ደም አፍስሶበት የመጣውን አሁን የከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነገር ከዚህ በፊት አይተን የማናውቅ ፍቅርና ዴሞክራሲ ላይ በትኩረትና በትዕግስት፣ ሌላውንም አክብሮ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው።’’  ያሉት ደግሞ የተባበረው  (ኦሮሞ ነጻነት ግንባር) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አባነጋ ጃራ ናቸው

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር  /ኦዴግ/ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ይህ ለውጥ ያመጣው በወጣቱ መስዋዕትነት መሆኑን ጠቅሰው   ለውጡን  መጠበቅም ያለበት እራሱ ወጣቱ ነው ብለዋል

የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ለደጋፊዎቻቸው፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባቶች ለወጣቶች መረጋጋትን፣ በሰከነ መንፍስ ነገሮችን መመልከት እንዲችሉ ምክር መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

”ዴሞክራሲ ነው በሚል ምክንያት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መንግስት ዝም ብሎ መመልከት አይገባውም” ያሉት አመራር አባላት በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲከበር ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ገልጸዋል።

ዴሞክራሲ ባህል አዳብሮ መብትና ግዴታን መረዳት “በአንድ ሌሊት የሚመጣ ነገር ባለመሆኑ መንግስት ጉዳዩን በቅርብ ሊከታተል ይገባል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በውጭ አገር የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉና በሀሳብ ልዕልና አሸናፊ ለመሆን በሚያስችላቸው መልኩ እንዲንቀሳቀሱ መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት ወደ አገራቸው እየተመለሱ ናቸው።