የተመቻቸላቸው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት የእውቀት ክፍተታቸውን ለማስተካከል እንደረዳቸው ተማሪዎች ገለጹ

108
ሰመራ መስከረም 4/2011 የሰመራ ዩኒቨርስቲ ባመቻቸላቸው በተግባር የተደገፈ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ያለባቸውን የእውቀት ክፍተት ለማስተካከል እንደረዳቸው  በአፋር ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ዩኒቨርስቲው ከ160 በላይ የአርብቶ አደሩን ልጆች በሳይንስ ዘርፍ በክረምቱ ሁለት ወራት የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠቱን ገልጿል፡፡ ከአፋምቦ ወረዳ የመጣችው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እሩቅያ ሀሰን  እንዳለችው በዩኒቨርስቲው በተሰጣት የማጠናከሪያ ትምህርት በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ያሉባትን የእውቀት ክፍተት ለማስተካከል አግዟቷል፡፡ በተያዘው የትምህርት ዘመን ለምትወስደው ክልላዊ ፈተና ብቁና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል ተወዳዳሪ ሆና ለመገኘት እንደሚያረዳትም ጠቅሳለች፡፡ ከዱብቲ ወረዳ የመጣው የአስረኛ ክፍል ተማሪው ሃቢብ አህመድ በበኩሏ  የማጠናከሪያ ትምህርቱ በመደበኛ ትምህርት ቤታቸው በንድፈ ሃሳብ ብቻ ተምረው እንደቆዩ ተናግራለች፡፡ ዩኒቨርስቲው ባመቻቸላቸው የማጠናከሪያ ትምህርት ያለፏቸውን የኬሚስትሪና ባዮሎጂ ትህምርቶች በቤተሙከራ ታግዞ የተሰጣቸው በመሆኑ የእውቀት ክፍተታቸውን ለማስተካከል እንደረዳት ነው ያመለከተችው፡፡ በተጨማሪም  በቀጣይ ለምትወስደው ብሄራዊ ፈተና እንድትዘጋጅ የጠቀማት መሆኑንም ጠቅሳለች፡፡ በዩኒቨርስቲ  የሁለት ወራት ቆይታቸው በሳይንስ ትምህርቶች ላይ የነበራቸውን እውቀት ይበልጥ ለማጎልበት እንዳገዛቸው የተናገረው ደግሞ ከአይሳኢታ ወረዳ የመጣው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ናስር ያሲን ነው፡፡ እንዲሁም ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ ተማሪዎች ጋር አብረው በመቆየታቸው  የእርስ በርስ መልካም ልምድና ተሞክሮ የተለዋወጡበት ቆይታ እንደነበርም ገልጿል፡፡ የዩኒቨርስቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ፣ጥናት፣  ምርምር ምክትል ፕሪዝዳንት አቶ መሃመድ አህመድ እንደገለጹት ተቋሙ ከአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ለመጡ   ከ160 በላይ የአርብቶ አደሩን ልጆች በሳይንስ ዘርፍ በክረምቱ ሁለት ወራት የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ይህም ተማሪዎቹ በቀጣይ ለሚጠብቃቸው ክልላዊና ብሄራዊ ፈተናዎች ተገቢውን እውቀት ጨብጠው የመወዳደር  አቅማቸውን ለማጎልበት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲልም የክልሉን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተንቀሳቃሽ ቤተ ሙከራ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም