ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የክልሉን የክረምት በጎ ፈቃድ መርሃግብር አስጀመሩ

216

ሀዋሳ (ኢዜአ) ሐምሌ 11/2014 የሲዳማ ክልል የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ መርሀ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት ዛሬ በአለታ ወንዶ ከተማ ተጀመረ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በአለታ ወንዶ ከተማ ተገኝተው የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት በማስጀመር መርሀ ግብሩን በይፋ ከፍተዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ አቶ ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተገኝተዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ መርሀ ግብር ከ567 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

ወጣቶቹ በክረምት የበጎፍቃድ አገልግሎት የአረጋዊያንና የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመገንባትና ከማደስ ባለፈ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በየአካባቢያቸው ችግኝ ይተክላሉ ተብሏል።

በተጨማሪም በመሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎች ወጣቱ በንቃት መሳተፍ እንዲችል መርሃ ግብር ተነድፎ ትግብራው መጀመሩ ተጠቁሟል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ካስጀመሩ በኋላ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን አረንጓዴ አሻራቸውንም አሳርፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም