‘ፀረ ሽብር ሕግ ማሻሻል ወይስ መሻር’ በሚለው ሃሳብ ላይ የተለያዩ ወገኖች የተለያየ ሃሳብ አላቸው

1028

አዲስ አበባ  መስከረም 4/2011  ‘በ2001 ዓ.ም የወጣው የፀረ ሽብር አዋጅ ለፍትህ ስርዓቱ መበላሸትና ለፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ምክንያት ሆኗል’ በሚል ከተለያዩ ወገኖች ትችት ሲያስተናግድ ቆይቷል።

መንግስትም ዕውነታውን በመገንዘብ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት ወደ ስራ ከገባባቸው አዋጆች አንዱ ይሄው አዋጅ ነው።

አማካሪ ምክር ቤቱ አዋጁ ‘ይሻር ወይስ ይሻሻል’ በሚል ረቂቅ ጥናት አቅርቦ ከተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረኮች እያካሄደ ይገኛል።

የሕግ ባለሙያው አቶ ወንድሙ ኢብሳና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የፀረ ሽብር ሕጉ ከመጀመሪያው ሲወጣም ምርጫ 97 በኋላ ለገዢው ፓርቲ የወጣ እንጂ ለበጎ ተግባር አልነበረም የሚል ሃሳብ አንጸባርቀዋል።

”አዋጁ በዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲከሰት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል” ብለዋል።

አዋጁን ለማሻሻል የተዋቀረው ንዑስ አጥኚ ቡድን ያቀረበው ሪፖርት አዋጁ በቅንነት እንደወጣ ተደርጎ መቅረቡን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።

ጋዜጠኞቹ ውብሸት ታዬና ኤልያስ ገብሩ በበኩላቸው አዋጁ ተጠቂ ካደረጋቸው ዘርፎች አንዱ ሚዲያና ጋዜጠኝነት እንደሆነ በማንሳት፤ አዋጁ ያደረሰውን ጉዳት ተናግረዋል።

ስለሆነም አዋጁ ‘መሻሻል ወይስ መሻር’ በሚለው ሃሳብ ላይ አቶ ዮናታን በአገሪቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በወንጀለኛ ሕጉ መመለስ ስለሚቻል አያስፈልገም ሲሉ፣ አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው የአዋጁ አብዛኛው ይዘቶቹ መሻሻል እንጂ የፀረ ሽብር ሕግ ግን አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና ኤልያስ ገብሩም አዋጁ የመረጃ ነጻነትን፣ ጋዜጠኞችን፣ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ፖለቲከኞችን ወይንም አንድ ቡድን ለማጥቃት በማይውል መልኩ መሻሻል እንጂ መሻር እንደሌለበት ተናግረዋል።

በሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት የፀረ ሽብር ሕግ ማሻሻያ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር ጌዴዎን ጢሞቲዎስ ባገኘነው መረጃ መሰረት ኮሚቴው እስካሁን የአዋጁ ይዘትና አተገባበር፣ በሕገ መንግስቱና ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አንጻር የሚቃኝ ጥናት ተደርጎ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል።

ጥናቱ በፌዴራልና ክልል በሚደረጉ የምክክር መድረኮቹ ግብዓቶች ተሟልተው እስከ መስከረም አጋማሽ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፤ በጥቅምት ወር አጋማሽ ደግሞ ለመንግስት እንደሚቀርብ ተጠቁሟል።

ኮሚቴው የካበተ ልምድ ያላቸው ጠበቆች፣ አማካሪዎች፣ የዩኒቨርሰቲና ምርምር ተቋማት ባለሙያዎችን በአባልነት አካቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከተለያዩ ወገኖች የሚነሱ የይሻር፣ ይሻሻል አማራጮችም ተለይተው የአዋጁ ዕጣ ፈንታም በጥቅምት ወር ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

 

—END—