የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን በዘላቂነት ለመግታት የሁሉም ድርሻ ወሳኝ ነው ተባለ

121
አዲስ አበባ   መስከረም 4/2011  የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታን በተመለከተ በሚስተዋለው መዘናጋት ሳቢያ የበሽታው ስርጭት እንዳይባባስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ። በትራንስፖርት ዘርፍ በተሰማራው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያለውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ  ተጋላጭነት ለመቀነስ እንቅስቃሴ እየተደረገ  መሆኑን የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል። የፌዴራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደሮች እና ተያያዥ ዘርፎች የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄዷል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ራቢያ ኢሳ እንደገለፁት በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ስርጭት የቆመ የሚመስላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ናቸው፤ ይህም ሲበዛ አደገኛ አመለካከት ነው። በመሆኑም የበሽታውን አሳሳቢነት በተመለከተ ተከታታይና የማያቋርጥ ግንዛቤ መፍጠር ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን የኮሚቴው ሰብሳቢ  ተናግረዋል። የበሽታውን ስርጭት በዘላቂነት ለመግታት በተለይ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩት የህብረተሰብ ክፍሎች የጎላ ሚና መጫወት ይችላሉ ሲሉም አመልክተዋል። የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ በበኩላቸው ባለስልጣኑ በሽታውን በተመለከተ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል እንቅስቃሴ በመደበኛነት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩና በትራንስፖርት ዘርፉ ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍና እንክብካቤ ከማድረግ ጎነ ለጎን ስርጭቱን ለመከላከል የሚረዱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን በመከላከል ረገድ የሚደረገው ጥረት እየተቀዛቀዘ በመሆኑ ስርጭቱን በዘላቂነት ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። “በትራንስፖርት  ዘርፍ የተሰማራው የህብረተሰብ ክፍል ከሌላው ጋር ሲነፃፀር የበሽታው ተጋላጭነት መጠኑ በሁለት እጥፍ ይበልጣል፤" ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። በጉባኤው ላይ የተሳተፈው “በትረ ሙሴ” የተሰኘው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው የጎንደር ነዋሪዎችን ያሰባሰበው ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ እሸቴ ሲሳይ ማህበራቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጠንካራ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል። ምክር ቤቱ ባለፉት 17 ወራት ባደረገው እንቅስቃሴ በትራንስፖርት ዘርፍ ለተሰማሩና ከኤድስ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩ 123 አዋቂዎች እንደዚሁም ወላጆቻቸውን በበሽታው ሳቢያ ላጡ 40 ህፃናት ከ 1ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ድጋፍ አድርጓል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም