ዶ/ር አቢይ በጅዳ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ

78
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በጅዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  አብይ  በሳዑዲ አረቢያ በህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ የሆነውን ታዳጊ መሀመድ አብዱልአዚዝን ከተኛበት ሆስፒታል ሄደው ጎብኝተዋል፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለሰ ዓለም እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ለዓመታት ታዳጊውን እያስታመሙ ያሉትን እናት አፅናንተው መንግስት ዜጋውን ለመደገፍ ሁሉንም ጥረት ያደርጋል ማለታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳዑዲ አልጋ ወራሽ ጋር ትናንት በተገናኙበት ወቅት የታዳጊውን ሁኔታ በማስረዳት ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቃቸውንና  ልዑሉ ይሁንታቸውን መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ  ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሳዑዲ ፈንድ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ልማቶችን በሚደግፍበት ሁኔታ ላይ ከኃላፊዎች ጋር  መምከራቸውም ተገልጿል፡፡ ቀደም ሲል ከሳዑዲ አልጋወራሽ ጋር ተወያይተው ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዲፈቱ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም