ክልሎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የያዙትን ዕቅድ ማሳካት አልቻሉም

58
አዲስ አበባ መስከረም 4/2011 የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ያቀዱትን ያህል አለመፈጸማቸውን ገለጹ። ለዕቅዱ አለመሳካት የበጀት እጥረት ዋነኛ ማነቆ መሆኑንም አስታውቀዋል። የክልሎቹ ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በሁለቱም ክልሎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሽፋን በተሻለ ደረጃ ይገኛል። ይሁንና በርካታ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው ማግኘት ባለመቻላቸው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ። አንዳንዶቹም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ችግሮች ይጋለጣሉ ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ እንዳሉት በክልሉ በአጠቃላይ ከ15 ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺ 96ቱ ብቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው። ክልሉ ባጋጠመው የበጀት እጥረትም ባለፉት ሁለት ዓመታት መገንባት የነበረበትን ትምህርት ቤት አለመገንባቱን ገልጸዋል።   የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር እሸቱ ከበደ በበኩላቸው በ2012 በክልሉ አንድ ሺ 200 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩ እቅድ የተያዘ ቢሆንም አሁን ያለው 783 ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት። ይህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በቀላሉ ማግኘት እንዳይችሉ አድርጓል። የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከባለሃብቶች በሚያሰባስበው ሀብት በተለያዩ ክልሎች የትምህርት ቤት እጥረት ያለባቸውን ቦታዎች በመለየት ትምህርት ቤቶችን እየገነባ ይገኛል። በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት የሚያስችል የግንባታ ማስጀመሪያ ስምምነት ትናንት በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና በክልሎቹ ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች መካከል ተፈርሟል። ትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ አድኣ ሊበን ወረዳና በጉጂ ዞን ሲሆን በደቡብ ደግሞ ሸካ ደቡብ ኦሞና ጌዲዎ ዞኖች ላይ ነው። ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረት ዋነኛ ተጎጂዎች ሴቶች ናቸው ይላሉ። ይህን ችግር ለማቃለልም ጽህፈት ቤታቸው እያከናወነ ያለውን ስራ ይናገራሉ።   ዶክተር እሸቱም  በዞኖቹ ባለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረት ምክንያት በተለይም ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ ነው ሲሉ የቀዳማዊት እመቤቷን ሀሳብ ይጋራሉ። የትምህርት ቤቶቹ ግንባታም በክልሎቹ ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እጥረት ያቃልላል ተብሎ  ይጠበቃል። ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር የተመደበ መሆኑም ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም