ፍቅርን፣ አብሮነትንና ይቅር ባይነትን በመላበስ አገራችንን ከችግር ለማውጣት መስራት ይገባናል - ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

202

ሐምሌ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጥላቻ ፋንታ ፍቅርን፣ በመለያየት ፋንታ አብሮነትን፣ ቂምበቀልን ሳይሆን ይቅር ባይነትን በመላበስ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን አገራችንን ከችግር ለማውጣት መስራት ይገባናል ሲሉ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ያስተማራቸውን 974 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

በስነ-ስርአት ላይ የተገኙት ዶክተር ቢቂላ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አስተሳሰባቸው ባልተለወጡ ሰዎች ብዙ መከራ አይታለች።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ቅን ልቦና ያላቸው ሚሊዮኖች ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጓት ተናግረዋል።

በመማር የተለወጠ ልብ በመያዝ በአንድነት በተባበረ መንፈስ ችግርን ለመፍታት እጅ ለእጅ መያያዝ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ተመራቂዎች የወገንን ችግር ለመፍታት መትጋት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በህብረብሔራዊ አንድነት የጸናች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን አምርሮ መታገል እንደሚገባም ገልፀዋል።

ተመራቂዎች በሚያከናውኑት ተግባር ብዙዎችን በማስከተል የተለወጠ ህብረተሰብ እንዲፈጠርም ተግተው እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጋረዳቸው ወርቁ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ዘንድሮ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስና በሌሎች 11 የትምህርት ክፍሎች በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር 974 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ ማስመረቁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም