በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ዱቄትና ብርድ ልብስ ድጋፍ አደረጉ

164

ደሴ ሐምሌ 9 ቀን2014 (ኢዜአ) ግሎባል አልያንስና አልማ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ዱቄትና ብርድ ልብስ ድጋፍ አደረጉ።
የአማራ ልማት ማህበር /አልማ/ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፋንታ ድጋፉን በማሻ ከተማ ተገኝተው ባስረከቡበት ወቅት እንደገለፁት ተፈናቃዮችን ለመደገፍ አልማ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሰራ ነው።
ሁሉም አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ በመተጋገዝ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ሊያልፈው እንደሚገባም አሳስበዋል።
የግሎባል አልያንስ ለኢትዮጵያውያን መብት የኢትዮጵያ አስተባባሪ አርቲስት ደሳለኝ ሀይሉ በበኩሉ ተፈናቃዮችን በመደገፍ እንዲቋቋሙ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል።
ግሎባል አልያንስም በውጭ ሀገር አስተባብሮ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 368 ኩንታል የምግብ ዱቄትና ሁለት ሺህ 530 ብርድ ልብስ ዛሬ ድጋፍ መደረጉን ገልጿል።
ተፈናቃይ ወገኖች በዚህ ወቅት የተሻለ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግም እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል።
ድጋፍን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው መንግስት ህብረተሰቡንና ድርጅቶችን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብና አልባሳት እንዲደርስ እየተደረገ ነው ።
ዛሬ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም የተፈናቃይ ወገኖች ዘርፈ ብዙ ችግር እንዲፈታ ሁሉም እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ከተለያዩ አካበቢዎች በወቅታዊ ችግር የተፈናቀሉ ከ36 ሺህ በላይ ወገኖች እንዳሉም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም