ለእድገታችንና ለብልጽግናችን ስኬት ታታሪና በእውቀት የበለፀገ ዜጋ ያፈልገናል… አቶ ፈንታ ደጀን

98

ጭሮ ፤ሀምሌ 9/2014ዓ.ም (ኢዜአ) ለእድገታችንና ለብልጽግናችን ስኬት በእውቀት የበለፀገ ዜጋ ያስፈልገናል ሲሉ የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ደኤታና የኦዳቡልም ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፈንታ ደጀን አስታወቁ።

ዩኒቨርስቲው ለአራተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 742 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ከተመራቂዎች መካከል 268ቱ ሴቶች ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በአራት ኮሌጆች በኢንጂነሪንግ፣ በግብርና እና መሬት አስተዳደር ዘርፍ በርቀትና እና ተከታታይ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ዛሬ ያስመረቀው ።

የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታና የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፈንታ ደጀን በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለፁት  የስራ ተነሳሽነትን የተላበሰ፣ ከስራ ፍላጎት ጋር ራሱን የሚያስማማ፣  ስራ ፈጣሪና  የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት የሚችል የተማረ የሰው ሀይል  ለሀገሪቱ ያስፈልጋል፡፡

ሀገር ወዳድና የህዝብ ራዕይ ያለው መንግስት ለመመስረት ለእድገትና ብልጽግና ስኬት የሚተጋ ታታሪና በእውቀት የበለፀገ ዜጋ እንደሚስፈልግ  ጠቁመዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትርና የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባል ክብርት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው  "ተመራቂዎች በስልጠና ያገኛችሁትን እውቀት ከእለት ተእለት ገጠመኝና በተለይ ደግሞ በጥናትና ምርምር  በማዳበር የህብረተሰቡን ችግር መፍታት ይጠበቅባችኋል" ብለዋል ።

"ዩኒቨርስቲው ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ የትምህርት መስኮችን በማስፋፋት በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን በማፍራት ላይ አትኩሮ መስራቱን ይቀጥላል" ያሉት ደግሞ  የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሙክታር መሀመድ ናቸው።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 3 ነጥብ 76 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችውና የመሬት አስተዳደርና ቅየሳ ትምህርት ክፍል ተማሪ መቅደላዊት ዘውዱ ያስተማራትን ህዝብ በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች ።

ከሀይድሮሊክስና ወተር ኢንጂነሪግ ትምህርት ከፍል 3 ነጥብ 92 በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ተማሪ ቃሲም ሁሴን በበኩሉ በሀገሪቱ የውሃ ሀብት ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደሚተጋ አስታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም