ተመራቂዎች በግል፣ በጥንድና በቡድን ሆነው በዪኒቨርስቲ ቆይታ ያገኙትን እውቀት ለስራ መፍጠሪያ ሊጠቀሙበት ይገባል

161

ሐምሌ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ተመራቂዎች በግል፣ በጥንድና በቡድን ሆነው በዪኒቨርስቲ ቆይታ ያገኙትን እውቀት ለስራ መፍጠሪያ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ መርሓ ግብሮች ያስተማራቸውን ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች እስመርቋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ምህረት ደበበና የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጣሰው ወልደሃና እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት መማር የባህሪ ለውጥ ማምጣት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲ የሀሳብ መፍለቂያ ቦታዎች፣ የአዳዲስ አስተሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ የተለያዩ ሀሳቦች ማስተናገጃ ቦታና የነጻነት ስፍራ ናቸውም ብለዋል።

ይህም በመሆኑ ተመራቂዎች የህዝብን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ ዲሞክራሲን የሚያጠናክር ሃሳብ እንዲያፈልቁ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ መከሰት የሌለባቸው ነገሮች ተፈጥረው የዜጎች ደም ፈሷል ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።

መማር ማለት የህዝብ ግንዛቤ ማሳደግ፣ የእይታ ከፍታ፣ ለመፍትሄ መረባረብ እንጂ ችግርን እያዩ እንዳለዩ ማለፍ አለመሆኑንም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን ከረሃብ፣ ከጦርነትና ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ ከተመራቂዎች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ ''ኢትዮጵያ በሰላምና በልማት ጎዳና እንድትጓዝ የሁላችን ድርሻ ያስፈልጋል'' ብለዋል።

መቻቻል፣ መነጋገር፣ መደማመጥ፣ የህዝቡን ስቃይ መረዳት ከሁሉም የተማረ ሰው የሚጠበቅ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ መንግስት የተመራቂዎቹን እውቀት መጠቀም የሚፈልግ ቢሆንም ለሁሉም ተመራቂ  ስራ መፍጠር የመንግስት ድርሻ ብቻ አይደለም ብለዋል።

በመሆኑም ተመራቂዎች በግል፣ በጥንድና በቡድን በመሆን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ልምድ በመጠጠቀም ስራ ፈጥረው ለሌሎችም ስራ መፍጠር እንዳለባቸው አሳሰበዋል።

መንግስት ለዚህም ይረዳ ዘንድ የመስሪያ ቦታ፣ የገቢያ ትስስርና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን የሚያደርግ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ''አገር በፈለገቻችሁ ጊዜ እንድትደርሱና በሙያችሁ ህዝቡን በፍትሃዊነት እንድታገለግሉ'' ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት በመተግባር ለሀገርና ህዝብ እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም