በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ቡድን በነገው ዕለት አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል

102
አዲስ አበባ መስከረም 4/2011 በአቶ ዳውድ ኢብሳ አያና የሚመራ ከፍተኛ የኦነግ አመራርና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሠራዊት አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም  ከተለያዩ  አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ወደ አዲስ አበባ እየገባ ነው ፡፡ በሊቀመንበሩ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን በነገው ዕለት አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የአቀባበል ኮሚቴ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው ህዝቡ ደስታውን ለመግለፅና ለድርጅቱ አመራር ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ከዋዜማው ጀምሮ በርካታ ህዝብ ወደ ፊንፊኔ እየገባ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ አመራሮቹ በቦሌ የአየር ማረፊያ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ሥነ ሥርዓቱ ወደሚካሄድበት መስቀል አደባባይ በማምራት መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት እንዲያበቃና ሃገሪቷ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ችግር በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ የዶክተር አብይ አህመድ አመራር በወሰደው ተነሳሽነት ድርድር ሲካሄድ ቆይቷልም ብሏል፡፡ ድርድሩ በሠላማዊና በተሳካ መንገድ ተጠናቆ ከፍተኛ የኦነግ አመራርና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሠራዊት በነገው ዕለት መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል፡፡ አቀባበሉም በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ተነግሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም