በጋምቤላ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግር ሊፈታ እንደሚገባ ተጠየቀ

64
ጋምቤላ  መስከረም 4/2011 በጋምቤላ ከተማና አካባቢው የኤሌክትሪክ አገልገሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈታ እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡ የክልሉ  የኤሌክትሪክ  አገልግሎት  የ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ አቅጣጫዎች   ዙሪያ ከባለድርሻ አካላትና ከሰራተኞቹ ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅት  እንደተገለጸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለደንበኞችን ተገቢው አገልግሎት እየሰጠ አይደለም። በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል አቶ ዲድሙ አደር በሰጡት አስተያየት መስሪያ ቤቱ ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት መስጠቱ በሪፖርቱ ያቅርብ እንጂ ለደንበኞች ያልተመለሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች እንዳሉ ተናግረዋል። በተለይም በጋምቤላ ከተማ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ከመኖሩ በተጨማሪ ለብልሽት ጥገናና አገልግሎት ፈላጊ ደንበኞች ፈጣን ምላሽ እንደማይሰጥ ጠቅሰዋል። ሆኖም  "መስሪያ ቤቱ ለአካባቢው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የጀመረው አዲስ ያልተማከለ የአደረጃጀት ለውጥ ጥሩ ነው" ብለዋል፡፡   ከሰራተኞች መካከል አቶ ሙሉጌታ ይማም በበኩላቸው ለደንበኞች የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋና ውጤታማ ሊሆን ያለቻለው በመስሪያ ቤቱ ይውስ  የመልካም አስተዳደር ችግር በመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለፃ የሰራተኛው ጥቅማ ጥቅምና  ደረጃ እድገት የመሳሰሉት መብቶቹ ባለተከበሩበት ሁኔታ የደንበኞች አገልግሎት ውጤታማ ሊሆን አይችልም። '' የሚሰራ ሳይሆን የማይሰራ ሰራተኛ ግንባር ቀደም እውቅና የደረጃ እድገት በሚያገኝበት መስሪያ ቤት ለደንበኞች የሚሰጠው አገልግሎት እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል'' በማለት የጠየቁት ደግሞ ሌለው የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ አቶ ቀና አየለ ናቸው። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጋምቤላ ክልል ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ቢቂላ ዋቅጅራ  ከደንበኞችና ከሰራተኞቹ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ  "በደንበኞችና በሰራተኞች የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግር ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል። በመስሪያ ቤቱ በደንኞችም ሆነ በሰራተኞች የተነሱ የውስጥና የውጪ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአዲሱ የመስሪያ ቤቱ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጥ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። "በተለይም የኃይል የመቆራረጥ ችግርና ለብልሽት ጥገና ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ አይደለም የተባለውን እንደ ክፍተት በመውሰድ በቀጣይ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ይሰራል "ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም