በሕዝብና መንግስት ትብብር የማይፈታ ችግር የለም-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

182

ሐዋሳ፤ ሐምሌ 8/2014 (ኢዜአ)፡ በሕዝብና መንግስት ትብብር የማይፈታ ችግር እንደማይኖር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሀገራዊ ፕሮጀክቶች ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወርቁ ጓንጉል ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት የሻሸመኔ ከተማ  የአቅመ ደካሞችና አረጋውያንን ቤት እድሳት ዛሬ አስጀምረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በመርሐ ግብሩ ላይ  እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማስጀመርና በመምራት  በተሰራው ሥራ በችግርና በጉስቁልና የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

በጎተግባሩንለማስቀጠል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሻሸመኔ ከተማ የ35 አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ቤቶችን አድሶ ለማስረከብ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርዓያ በመከተል በጎ ተግባሩን መፈጸም መጀመራቸውን አመልክተው፤ ''ዛሬ አፍረሰን ብቻ የምንሄድ ሳይሆን ቤቶቹ ተመርቀው ስራ ላይ መዋላቸውን እናበስራለን ''ብለዋል።

ይሄም  መንግስትና በሕዝብና መንግስት ትብብር የማይፈታ ችግር እንደሌለ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣዮቹ ሁለት ቀናትም በምዕራብ አርሲ ዞን ሁለት ወረዳዎች ቤተሰቦቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ  ተማሪዎች የ7 ሚሊዮን ብር የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍና የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ውሾ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው በጎ ስራ በተለይ ጧሪና ረዳት ያጡ አረጋዊያንና ህጻናትን ከመንገድ ላይ ጭምር በማንሳት የቤት ባለቤት በማድረግ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት  አሰታዋሽ  ላጡና በከፋ  ድህነት ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያን ቤት ለመስራት ከተማዋን በመምረጣቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በከተማዋ ከሁለት ዓመት በፊት ተነስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ  በርካታ ቤቶችና የንግድ ህንፃዎች ውድመት ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ የከተማው አስተዳደር፣ነዋሪውና የሌላው አካባቢ ህዝብ ባደረገው ድጋፍ በአጭር ጊዜ ከ800 በላይ ቤቶች ተገንብተው የጉዳቱ ሰለባ ዜጎች ተመልሰው እንዲቋቋሙማድረጉን አስረድተዋል።

በከተማዋ የቤት እድሳቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አረጋሽ ወልደመስቀል እና አቶ ወልደሚካኤል ሳቀቶ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በፊት የሚኖሩበት ቤት በእርጅና ምክንያት በላያቸው ላይ እየፈረሰ ሲቸገሩና ሲጎሳቆሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ አዲስ ቤት ሊሰራላቸው በመሆኑ ዳግመኛ የተወለዱ ያህል ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፤ ለመንግስትና ለተባበሯቸው አካላት  ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመረሐግብሩ ላይ ሚኒስትሮችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ቤት በማደስ ተግባሩ ላይ 16 የፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም