በከተማ ግብርና ሥራችን አቅመ ደካሞችን እየደገፍን የሕብረተሰቡን የሥራ ባህል እናሳድጋለን---የወጣቶች ሊግ

147

ሀዋሳ (ኢዜአ) ሐምሌ 8/2014 በተሰማሩበት የከተማ ግብርና ሥራ አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ባለፈ የህብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር እየሰሩ መሆናቸውን በሃዋሳ ከተማ የወጣቶች ሊግ አደረጃጀቶች ገለጹ።

ወጣቶቹ በየክፍለ ከተማቸው ባሉ ክፍት መሬቶች ላይ የጓሮ አትክልቶች በማልማት የከተማ ግብርና ስራው ውጤታማ እንዲሆን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ትናንት በሲዳማ ክልልና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ስራቸው የተጎበኘላቸው ወጣቶች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፣ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በየክፍለከተማው ባሉ ክፍት ቦታዎች ላይ የከተማ ግብርና ሥራ ጀምረዋል።

በእዚህም በየቀበሌው ያሉ አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ባለፈ የህብረተሰቡን አስተሳሰብና የሥራ ባህል ለመቀየር እየሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በሀዋሳ ከተማ የምስራቅ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ሊግ ፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ወጣት መለሰ አለማየሁ እንዳለው ወጣቱ እንደሃገር የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲረጋገጥ በተለያየ ዘርፍ ተሳትፎውን ማሳደግ አለበት፡፡

"ምግቤን ከጓሮዬ" በሚለው ሃገር አቀፍ ንቅናቄ መነሻ በክፍለ ከተማው ከ713 በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ  ከ2 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የከተማ ግብርና ስራ ለማከናወን እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

የክፍለ ከተማው ወጣት ባለፉት ሁለት ወራት ህብረተሰቡ በየእለቱ የሚጠቀማቸውን የጓሮ አትክልቶች በማልማት ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግሯል።

"ልማቱ በህብረተሰቡ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል በመሆኑ የማህበረሰቡን አመለካከት ለመለወጥ ቀጣይነት ያለው ሥራ ይስራል" ብሏል።

የደረሱ አትክልቶችን ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችና አረጋዊያን በማከፋፈል ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው ወጣት መለሰ የገለጸው።

በከተማው የመሃል ክፍለ ከተማ የወጣቶች ሊግ ፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊው ወጣት አዳነ ከፋ በበኩሉ በክፍለከተማው ባሉ ሦስት ቀበሌዎች ወጣቶች በከተማ ግብርናው የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግሯል።

"ባለፉት ሁለት ወራት በቀበሌና በተለያዩ ተቋማት ግቢ ውስጥ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ጎመንና ቃሪያ በማልማት ውጤታማ ሆነናል" ብሏል።

ስራው ከዚህ ቀደም ጦማቸውን በሚያድሩ መሬቶች ላይ እየተከናወነ ያለ በመሆኑ በአካባቢው ነዋሪ ላይም መነሳሳትን መፍጠሩን ተናግሯል።

እንደወጣት አዳነ ገለጻ፣ የክፍለ ከተማው ወጣት በከተማ ግብርናው ላይ ከሚያደርገው ተሳትፎ በተጨማሪ የህብረተሰቡን ተሳፎ የማሳደግ ሥራ እየሰራ ነው።

ለእዚህም የክፍለ ከተማው ወጣቶች በክፍት መሬቶች ላይ ከሚያደርጉት የአትክልት ልማት በተጨማሪ በግለሰብ ደረጃ የሚከናወኑትን ጭምር እየደገፉ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሷል።

በሐይቅ ዳር ክፍለ ከተማ ጉዱማሌ ቀበሌ ውሃ ልማት ግቢ ውስጥ በወጣቶችና ሴት አደረጃጀቶች የከተማ ግብርና ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑ የገለጸው ደግሞ የክፍለ ከተማው ወጣቶች ሊግ አመራር ወጣት አየለ ሳቃቶ ነው።

በቀበሌው ብቻ 600 ወጣቶችና ሴቶች ከ400 ካሬ በላይ በሚሸፍን ቦታ ላይ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ቃሪያና ሌሎች አትክልቶችን እያለሙ መሆኑን ተናግሯል።

እንደ ወጣቱ ገለጻ በክፍለ ከተማው ጥቅም ሳይሰጡ የተቀመጡ ክፍት ቦታዎች ተለይተው የከተማ ግብርና ሥራ እየተከናወነባቸው ይገኛል።

በከተማው በክፍት መሬቶች ላይ የተጀመረው የከተማ ግብርና ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ወጣቶቹ ጠይቀዋል።

ሥራው የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ከመፍጠር ባሻገር የማህበረሰቡን የሥራ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ስለሚቀይር አጠንክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በተለይ በማህበረሰቡ ውስጥ የልማቱን ጠቀሜታ በማስረጽ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታ ላት አተኩረው አንደሚሰሩ ነው የገለጹት።

"ምግቤን ከጓሮዬ" የሚለውን ንቅናቄ ተከትሎ እንደ ሀዋሳ ከተማ ከ32 ሄክታር በላይ መሬት በከተማ ግብርና እየለማ መሆኑን ኢዜአ ቀደም ሲል መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም