የግጭት መከላከያ ማጎልበቻ የምክክር መድረክ በሶዶ ከተማ ተጀመረ

82
ሶዶ መስከረም 4/2011 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና የቅርስ ተንከባካቢ ማህበር በጋራ ያዘጋጁት የተቀናጀ ዘመናዊና ባህላዊ የግጭት መከላከያ ማጎልበቻ የምክክር መድረክ ዛሬ በሶዶ ከተማ ተጀመረ፡፡ ምሁራንን ፣የሃገር ሽማግሌዎች ፣የኃይማኖት መሪዎች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በምክክር መድረኩ እየተሳተፉ ነው፡፡ መድረኩን በምርቃት የከፈቱት የአካባቢው ሃገር ሽማግሌዎች ሃገር ችግር ላይ ስትወድቅ ተመካክሮ መፍታት የተለመደ ቢሆንም በቅርቡ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ላይ መዘናጋት እንደታየ ተናግረዋል፡፡ ይህም ዋጋ ማስከፈሉን ነው ሽማግሌዎቹ የገለጹት፡፡ በተለይም ወጣቱ ነባሩን የመቻቻል እሴት ጠብቆ እንዲያቆይ የተቀናጀ የግጭት መከላከል ላይ ያተኮረ መድረክ መዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ወጣቱ የተለመደውን እሴት ጠብቆ እንዲያቆይ ማስተማር ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በአዲሱ የስራ ዘመን ያለፈውን በመርሳት ያሉንን ጸጋዎች በተገቢው በመጠቀም ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ መሰራት እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡ ሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶችን በማሳተፍ ባለመሰራቱ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትና አሁን የተገኘውንም ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ የወላይታ ባህልና ቅርስ ተንከባካቢ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዩኤል ሄራሞ በበኩላቸው ግጭት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ሰላምና ልማትን እንዳያደናቅፍ መሰረታዊ ችግሮችን ማወቅ የሚያስችል መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግጭቶችን በበሰለና በዘመናዊ መልኩ ለመፍታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመጠቆም ከአባቶችና ኃይማኖት መሪዎች ጋር የሚደረገው ውይይት ጠቃሚ  መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር ወንድሙ ወልዴ ናቸው፡፡ ዘመናዊና ባህላዊውን የግጭት አፈታት ዘዴ ለማዋሃድ እውቀት የሚያስገኝ መድረክ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የወይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው የወላይታ ህዝብ የውስጥ አንድነቱን በማጠናከር ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እሴቶቻችን ላይ ለመስራት የሃገር ሽማግሌዎችን በማደራጀት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ "የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች ያላቸውን ነባር እውቀት ከዘመናዊው ጋር በማዋሃድ የተቀናጀ የግጭት አፈታት ስልት ለመንደፍ መድረኩ መልካም አጋጣሚ ነው "ብለዋል፡፡ ከአጎራባች ዞኖችና ህዝቦች ጋር ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡ በመድረኩ የዘመናዊና ባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓትና ፣በወላይቲኛ ቋንቋ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም