ምክር ቤቱ ውስን ዓላማ ለማሳካት ስለሚደረግ የድጎማ በጀት እና የፌዴራል መሰረተ-ልማት ሥርጭት ፍትሃዊነት የክትትል ሥርዓት ለማስፈጸም የተዘጋጀ ደንብ አፀደቀ

255

ሐምሌ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነ ዓላማ ለማሳካት ስለሚደረግ የድጎማ በጀት እና የፌዴራል መሰረተ ልማት ሥርጭት ፍትሃዊነት የክትትል ሥርዓት ለማስፈጸም የተዘጋጀ ደንብ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ስድስተኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አጠናቋል።

በመድረኩም ውስን ዓላማ ለማሳካት ስለሚደረግ የድጎማ በጀት እና የፌዴራል መሰረተ-ልማት ሥርጭት ፍትሃዊነት የክትትል ሥርዓት ለማስፈጸም በተዘጋጀ ደንብ ላይ ውይይት አድርጎ አጽድቋል።

የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ኃይሉ ኢፋ ደንቡ ምክር ቤቱ በሕገ-መንግሥቱ የተሰጠውን የሃብት ክፍፍል ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ እና መንግሥታዊ ኃላፊነት በተገቢ መንገድ መወጣት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሚኖሩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል የመልማት ዕድል እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።

የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እና የግልጸኝነትና የተጠያቂነት ሥርዓት ያሰፍናል ነው ያሉት።

ደንቡ በፌዴራል የሥልጣን ወሰን ውስጥ በክልሎች መሰረተ-ልማት ዝርጋታን በሚያከናውኑ የፌዴራል ተቋማት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች በሚሰጠው ውስን ዓላማ ያላቸው ድጎማዎች ተብለው በተለዩ ሃብቶች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1263/2013 ለማስፈጸም የተዘጋጀ ደንብም አፅድቋል።

እንዲሁም ሕገ-መንግሥታዊ ትርጉም ጋር የተያያዙ 87 ጉዳዮች ላይ በመወያየት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አፅድቋል።

በዚህም መሰረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከቀረቡለት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ብቻ ሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜ ያስፈልገዋል በማለት ውሳኔ ተላልፏል።

በተመሳሳይ 80 የሚሆኑ ጉዳዮች ሕገ-መንግሥታዊ ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ አሳልፏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም