የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለማስቆም የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ማገዝ አለበት – የተመድ ዋና ፀኃፊ

1047

አዲስ አበባ መስከረም 4/2011 በደቡብ ሱዳን ዓመታት ያስቆጠረውን የእርሰ በርስ ግጭት ለማስቆም ሰሞኑን የተፈረመው የሰላም ስምምነት ውጤታማ እንዲሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አሳሰበ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) አባል አገሮች 33ኛው የመሪዎች ጉባኤ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር የመጨረሻ የሰላም ስምምነት ፈርመዋል።

የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ”ሁለቱ ወገኖች አምስት ዓመታት ያስቆጠረውን ግጭት ለመቋጨት ይቻል ዘንድ የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን አድንቀው፤ ለተግባራዊነቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትብብር መስራት አለበት” ብለዋል።

ስምምነቱ የደቡብ ሱዳን ምድር የራቀውን ሰላም ለመመለስ የሚያስችል ትርጉም ያለው እመርታ መሆኑን ዋና ፀኃፊው ገልፀዋል።

የደቡብ ሱዳን ህዝብ በስተመጨረሻ ላይ የሚገባውን የሰላም አየር መተንፈስ ይችል ዘንድ የስምምነቱ ፈራሚዎችም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉና አካታች በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጉተሬዝ አሳስበዋል።

ከመላው ደቡበ ሱዳን ጥላቻ እንዲወገድ ለማድረግም ሁሉም  የሚመለከታቸው የአገሪቱ የፖለቲካ ቡድኖች ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

የሰላም ስምምነቱ እውን እንዲሆን አስተዋፅኦ ላደረጉት የቀጠናው አገሮችና ሌሎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካላት ዋና ፀኃፊው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

”ይሁንና የደቡብ ሱዳን ዜጎች የሰላም አየር በመተንፈስ ወደ ልማት እንዲሸጋገሩ ስምምነቱ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ ተመድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ዋና ፀሀፊው፤ ለስምምነቱ ስኬት ድርጅቱ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ህብረት ጋር በጋራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በደቡብ ሱዳን ያለው አሳሳቢ ሁኔታ አሁንም ሊቀጥል የሚችል በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በተቀናቃኞቹ መካከል በቆየው ግጭት ሳቢያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ህይወት አልፏል፤ ሚሊዮኖች ደግሞ ለረሃብ፣ መፈናቀልና ስደት ተዳርገዋል።

ተቀናቃኖቹ እአአ በ2015 ግጭቱን ለማስቆም ያስችላል የተባለ የሰላም ስምምነት ፈርመው የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ ተስኗቸዋል።