የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ

3250

አዲስ አበባ መስከረም 4/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)  ምክር ቤት ከዛሬ ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን እንደሚያካሂድ ባስታወቀው መሰረት ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ምክር ቤቱ በሚያካሂደው ስብሰባ ባለፈው ሳምንት በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተገመገሙና ለምክር ቤቱ እንዲቀርቡ የተወሰኑ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።

ምክር ቤቱ ድርጅቱ ከመስከረም አጋማሽ በኋላ በሚካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የሚቀርብ ሪፖርት ላይ እንደሚወያይም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በወቅታዊ ድርጅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡