አሸባሪው ሸኔ ንጹኃንን በመጨፍጨፍ ህዝብና መንግስትን ለመነጠል የሚያደርገው ሙከራ አይሳካለትም

63

ሐምሌ 06/2014(ኢዜአ)አሸባሪው ሸኔ ንጹኃንን በመጨፍጨፍ ህዝብና መንግስትን ለመነጠልና የብሄር ግጭት ለመፍጠር የሚያደርገው ሙከራ እንደማይሳካለት የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ታምሩ ተናገሩ።

አሸባሪው ሸኔ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞኖች በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ በንጹሃን ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፈፀሙ ይታወቃል።

የሽብር ቡድኑ በፈፀመው ጥቃት በርካታ ንጹሃን ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን የአካልና የስነልቦና ጉዳትም ደርሷል፤ ንብረታቸውም ወድሟል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ታምሩ፤ አሸባሪው ሸኔ በሀገራዊ ለውጡ የተፈጠረውን ሰላማዊ ፓለቲካዊ ትግል ወደ ጎን በመተው በምዕራብ ኦሮሚያ ጫካ ገብቶ በንጹሃን ወገኖች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን በግፍ መግደሉንና በንብረት ላይም ውድመት ማድረሱን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በርካታ የጤና፣ የትምህርትና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሽብር ቡድኑ መቃጠላቸውንም እንዲሁ።

ባለፉት ዓመታትም በኦሮሞ ህዝብ ስም እታገላለሁ እያለ የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎችን ሳይቀር በመግደል የለየለት ሀገር አጥፊ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።

ትውልድ የሚታነጽባቸውን ትምህርት ቤቶች ጨምሮ የበርካታ አርሶ አደር መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠል ማውደሙን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ በምዕራብ ወለጋ ዞን በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎችም ለፖለቲካ ዓላማው ሲል የኦሮሞ፣ የአማራ እና የጉምዝ ማህበረሰቦች ላይ ጭፍጨፋ በመፈጸም በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ መሞከሩን ገልጸዋል።

ንጹኃንን በመጨፍጨፍ ህዝብና መንግስትን ለመነጠልና የብሄር ግጭት ለመፍጠር  የሚያደርገው ሙከራ ግን መቼም እንደማይሳካለት ነው የተናገሩት።

የሽብር ቡድኑ ላይ ጠንካራ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው በዚህም ብዙ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል ብለዋል።

ለተጎዱት ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንና ይህም ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም