ኬኒያ ሀገር በቀል የተሸከርካሪ መገጣጠሚያዎችን የሚያሳድግ ምክር ቤት ልታቋቁም ነው

497

ሐምሌ 06/2014(ኢዜአ) የኬንያ መንግስት የአውቶሞቲቭ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ አውቶሞቲቭ ምክር ቤት እንደሚያቋቁም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ገለፁ።

ኬንያታ ይህንን የተናገሩት በናይሮቢ ዩሮ 4 ሚትሱቢሺ ኤል 200 ፒክ አፕ የተሰኘ አገር በቀል መገጣጠሚያ ፋብሪካ በተከፈተበት ወቅት ነው።

ፕሬዝዳንት ኬንያታ የኢንደስትሪው ባለድርሻ አካላት የአውቶሞቲቭ ዘርፉን የማነቃቃትና የማረጋጋት አላማውን ከዳር ለማድረስ ከመንግስት ጋር ተባብረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት ዘርፉን ለማሳደግ ላደረጉት ጥረትም አመስግነዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢንደስትሪላይዜሽን ዋና አስተዳዳሪ ዋና ጸሐፊ ዴቪድ ኦሲያኒ እንደተናገሩት የብሔራዊ አውቶሞቲቭ ፖሊሲ ትግበራ አገሪቱ እንደ ክልላዊ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ማዕከልነት ቦታዋን እንደምትመልስ ያረጋግጣል።

የሀገሪቱ የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በአሁኑ ጊዜ በዓመት 30 ሺህ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ቢኖራቸውም 6 ሺህ ክፍሎችን ብቻ እንደሚገጣጥሙ ገልፀዋል፡፡

ለማቋቋም የታሰበው አውቶሞቲቭ ካውንስል(ምክር ቤት) ይሄንና መሰል ችግሮች ይቀርፋል ተብሎ እንደሚገመት ዘገባው አትቷል፡፡

ኢንዱስትሪው 100 ሺህ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ለኬንያውያን የስራ እድል መፍጠር መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

ኢንዱስትሪው በዓመት 30 ቢሊየን የሚጠጋውን ግብር ለመንግስት ገቢ እንደሚያደርግ የሲጂቲኤን ዘገባ ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም