ኢትዮጵያ የዶራሌህ ወደብ የቀንድ ከብት ማቆያ ተርሚናልን ለመጠቀም ከጂቡቲ ተስማማች

74

ሐምሌ 06 ቀን 2014 ዓ.ም(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በጂቡቲ የሚኘው የዶራሌህ ወደብ የቀንድ ከብት ተርሚናልን መጠቀም የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከጂቡቲ መንግስት ጋር ተፈራረመች።

ስምምነቱን ግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን ከጂቡቲው የግብርና፣ የውኃ፣ የዓሣ፣ የቀንድ ከብት እና የባህር ሀብት ሚኒስትሩ ሞሐመድ አሕመድ አዋሌህ ጋር ተፈራርመዋል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ግብርና ሚንስትር አቶ ዑመር ሁሴን፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብት ቀዳሚ ሀገር እንደመሆኗ የወጭ ንግድን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።

ለእንስሳት ማቆያነት የሚያገለግለው ወደቡ አገሪቱ ደህንነቱ እና ጥራቱ የጠበቀ አቅርቦት እንዲሁም ቀጥተኛ ወጪ ንግድን በማረጋገጥ ረገድ እየገጠማት ያሉትን እንቅፋቶች እንደሚቀንስ አመልክተዋል።

የጅቡቲ የግብርና፣ የውሃ፣ አሳ ፣ እንስሳት እና ባህር ሀብት ሚኒስትር መሀመድ አህመድ አዋሌህ በኢትዮጵያ እና ጂቡቲ መካከል ያለው የንግድ ትሥሥር እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የጅቡቲ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት በአፋር ክልል በሚገኘው የሚሌ ደረጃውን የጠበቀ የኳራንቲን ተቋም ግንባታ ላይ ኢንቨስት ማድረጉ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ማቆያው ለጂቡቲ ወደብ አቅራቢያ መሆኑ በዘርፉ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሁለቱ አገራት የግብርና ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች በተገኙበት የፊርማ ስነ ስርዓቱ ተካሂዷ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም