በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ የሚታዩ ስህተቶችን ለመቀነስ የባለሙያዎችን የተግባቦትና የሙያ ክህሎትን ማጎልበት ያስፈልጋል

113

አዲስ አበባ  ሀምሌ 6/2013 /ኢዜአ/ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ የሚታዩ የሕክምና ስህተቶችን ለመቀነስ ለባለሙያዎች የተግባቦትና የሙያ ክህሎት ሥልጠናዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተጠቆመ።

የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ወቅት በሚያጋጥሙ የሕክምና ስህተቶችና የስነ-ምግባር ግድፈቶች ዙሪያ ከጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በሕክምና ስህተት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የሚቀበለው የጤና ባለሙያዎች የስነ-ምግባር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ገላኔ ሌሊሳ፤ ለኮሚቴው እየቀረቡ ያሉ የህክምና ስህተት ቅሬታዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ኮሚቴው ከተቋቋመበት 2007 ዓ.ም. ጀምሮ 216 የሕክምና አገልግሎት ስህተትን የተመለከቱ ቅሬታዎችን መቀበላቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 131 በግል ጤና ተቋማት 74 ደግሞ በመንግሥት ጤና ተቋማት ላይ የቀረቡ ሲሆኑ 116 ቅሬታዎች ውሳኔ ማግኘታቸውን ጨምረዋል።

የሕክምና ባለሙያዎች የተግባቦት ክፍተት፣ የታካሚውን የሕመም ታሪክ በደንብ ሰንዶ አለመያዝ፣ አሰራሩ ዘመናዊ አለመሆንን የህክምና ስህተት ቅሬታዎች እየጨመሩ እንዲመጡ ማድረጉን ተናግረዋል።

የተግባቦት፣ የሕይወት ክህሎትና ሌሎች ሥልጠናዎችን በተከታታይነት በመስጠት በሕክምና ስህተት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን መቀነስ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሕክምና ባለሙያዎችም በሙያተኞች ዘንድ የህክምና አሰጣጥ ችግሮች መኖራቸውን በማመን ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ታደሰ አጥላባቸው፤ በጤና ተቋማት በቸልተኝነትና በክህሎት ማነስ የህክምና ስህተት እንደሚፈጠር አንስተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከክህሎት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በጤና ተቋማት ላይ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለማቅረብ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በመጥቀስ የሙያ ማህበራት፣ የሕክምና ተቋም ኃላፊዎችና ሙያተኞች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም