በከተማው ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ የወጣቶች ማዕከል ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

79

ጂንካ (ኢዜአ) ሐምሌ 5/2014 በጂንካ ከተማ ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

ማዕከሉ ወጣቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው ላይ በጋራ የሚመክሩበትና የተለያዩ ልምድና እውቀቶችን የሚቀስሙበት መሆኑም ተመላክቷል።

ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ማዕከል ቤተ-መጻህፍት፣ የስዕል አውደርዕይና ቴአትር ማሳያ ክፍሎች እንዲሁም የመሰብሰቢያ አዳራሽን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ 13 ክፍሎች አሉት።

ለማዕከሉ ግንባታም ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መዳረጉም በምርቃ ስነስርአቱ ላይ ተገልጿል።

ማዕከሉን የመረቁት የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንዳሉት፣ ከአጠቃላይ ህዝብ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ ትውልድ ለዚህች አገር ዕድገትም ሆነ ወደኋላ መቅረት አስተዋጽኦው የጎላ ነው።

"በሀገሪቱ ወጣቱ ትውልድ ሙሉ አቅሙን እና ዕውቀቱን ተጠቅሙ ወደልማት ቢሰማራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይቻላል" ብለዋል።

በጂንካ ከተማ የተገነባው የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከል ወጣቶች ችግር ፈቺ ሀሳቦችንና የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያፈልቁ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

እርስ በርስ ሀሳብ በመለዋወጥ የተሻለ እውቀት የሚገበያዩበት ጭምር መሆኑንም ነው አቶ ንጋቱ ያመለከቱት።

ማዕከሉ ለወጣቱ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ በዞኑ በኩል የተለያዩ ቁሶችን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትም የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ማዕከሉን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግም መኮንን በበኩላቸው፣ በማዕከሉ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ስብዕና መገንባት የሚያስችሉ ግልጋሎቶች የሚሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዞኑ የሚገኙ ወጣቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው ላይ በጋራ የሚመክሩበትና የተለያዩ ዕውቀቶችን እና ልምዶችን እርስ በእርስ የሚለዋወጡበት ነው" ብለዋል።

ማዕከሉ ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ መስሪያዎች፣ የመወያያና የቴአትር ማሳያ አዳራሾች እንዲሁም የስዕል አውደርዕይ ማዘጋጃ ክፍሎች እንዳሉትም ተናግረዋል።

"ከእዚህ በተጨማሪ ቤተ-መጻህፍት፣ የኮምፒውተር ማሰልጠኛ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና መማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ 13 የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ክፍሎችን አካቷል" ብለዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ግዳጁ ጎሮጊ ወጣቱን በሀገሩ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ ለማድረግ ስብዕና በመልካም መገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግሯል።

ዛሬ የተመረቀው ማዕከልም ወጣቱ እርስ በእርስ የሚማማርበትና የእውቀት ሽግግር የሚያደርግበት ብቻ ሳይሆን ሞጋችና በምክንያታዊ አስተሳሰብ የተቃኘ ብቁ ዜጋ እንዲሆን ለማድረግ ያግዛል ብሏል።

ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን አላስፈላጊ ቦታዎች ላይ ከሚያውሉ ወደማዕከሉ በመምጣት ስብእናቸውን እንዲገነቡም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም