በኢትዮጵያ በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ የሕንድ ባለሃብቶች እየተሳተፉ ነው- በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር

80

ሐምሌ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ የሕንድ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሮበርት ሽሪን ሮበርት ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሽሪን ሮበርት፤ የሕንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆኑ የውጭ ባለሃብቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሕንድ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ አገሪቷ በፈጠረችው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ሌሎች የሕንድ ባለሃብቶችም ወደ ኢትዮጵያ ትኩረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የነበራቸው የሕንድ ኩባንያዎች ወደ 650 የሚጠጉ ሲሆኑ፤ ከ3 እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው መሬት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

የሕንድ ኢንቨስትመንት 62 በመቶው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲሆን በመቀጠል ግብርናው ከአጠቃላይ 13 ነጥብ 1 በመቶው ነው።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እንኳን ወደ 35 የሚጠጉ የህንድ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የሕንድ ኩባንያዎች በእርሻና በአበባ ልማት፣ በኢንጂነሪንግ፣ በፕላስቲክ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በጥጥ እና ጨርቃጨርቅ፣ በውሃ አስተዳደር፣ በፋርማሲዩቲካል እና በጤና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

ሕንድ ለኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ትልቅ የንግድ አጋር ስትሆን 10 ነጥብ 2 የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ትሸፍናለች ሲሉም ገልጸዋል።

በ2021 በኢትዮጵያ እና በሕንድ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ንግድ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ 75 ነጥብ 13 ሚሊየን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም