የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሸንፍ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ መሸነፍን መቀበል አለበት-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

87
አዲስ አበባ መስከረም 3/2011 የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሸንፍ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ መሸነፍን መቀበል አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ሰንደቅ ዓላማን ጨምሮ ማንኛውንም ሀሳብ በፓርላማ ውይይት ተደርጎበት ሁሉን አቀፍ የሆነው ሀሳብ እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑንም አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ አገር እየገቡ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የአሸናፊነት ስሜት እንዲሰማቸው እንፈልጋለን ብለዋል። ይሁንና አሸናፊነትና መሪነት የተለያዩ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሸንፍ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ መሸነፍን መልመድ አለበት ብለዋል። ከህዝባችን ጋር ሆነን ያመጣነው ለውጥ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይበቃል ያሉት ዶክተር አብይ በመግደል ብቻ ሳይሆን በፍቅር ማሸነፍ እንደሚቻል ለማሳየት ነው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ኤርፖርት ድረስ ሄደን የምንቀበላቸው ብለዋል። ድርጅቶቹ አሸናፊነታቸውን ከሳቱ እንደተለመደው ተሸናፊ መሆናቸው የማይቀር መሆኑንም አመልክተዋል። ''በረባው ባልረባው ጉዳይ ጉልበቴን አሳያለሁ አሸናፊነቴን አሳያለው  እያለ የሚፍጨረጨር ሃይል ካለ እንደ ሳውዝ ሱዳን እንደ ሶማሊያ እንሆናለን።ማንም አያሸንፍም የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሸንፍ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ ካለ መሸነፍን መልመድ አለበት።ሰጥቶ መቀበልን መልመድ አለበት ብቻዬን አሸናፊ ልሁን የሚል ሀሳብ ለአንድ ሳምንት በጉልበት ሊያሸንፍ ይችላል ሌላ ተረኛ ሲመጣ ደግሞ ይሸነፋል።እየተሸናነፍን ከምንኖር በጋራ እናሸንፍ ያልንበት ምክንያት ይሄ ነው።'' እንሰብሰብ ስንል ብዙዎች እንጨፍለቅ ያልን ይመስላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድነት አንድ አይነትነት አለመሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸውን አስታውሰዋል። በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በሰንደቅ ዓላማ ምክንያት እየታየ ያለውን አለመግባባት በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል። ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ሳይሆን የትኛውም ሀሳብ ፓርላማ ውስጥ ይስተናገድ እያልን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉን አቅፎ የሚሄደውና አሸናፊ የሆነው ሀሳብ ይቀጥላል ብለዋል። ''ባንዲራ የሀሳብ መግለጫ ማሳያ አርማ ነው።የፓርቲዎች አርማ ነው።የፓርቲዎች አርማ የእነርሱን እሳቤ የሚገልጹበት አንዱ መንገድ ነው።በጽሁፍ ይገለጻል በአርማ ይገለጻል በሞቶ ይገለጻል በህገ ደንባቸው ይገለጻል።በንግግራቸው በአሰራራቸው ይገለጻል አንዱ መግለጫ ነው።እኛ ምንድነው ያልነው።ማንም ሰው በሰላማዊ መንገድ መጥቶ በሀሳብ ልዕልና ማሸነፍ ይችላል ብለናል ባንዲራን ይጨምራል ሌላ ጉዳይ ነው።ችግር የለውም ባንዲራ በጣም ቀላል ነገር ነው ብዙ ዓለም ላይ ባንዲራ እየተቀያየረ ነው የኖረው።የአሜሪካ ባንዲራ ዛሬ የምናየው አስራ ሶስት ጊዜ ተቀይሯል።ሲጀመር አንድ ኮከብ አልነበረውም።አግድም ብቻ ነው የነበረው። እየዋለ እያደረ ስቴት ሲጨመር ኮከቡ ተጨምሮ ዛሬ እንደምታዩት ሀምሳ ደርሷል።የኛም ባንዲራ መላው የኢትዮጰያ ህዝብ የሚፈልገው ከሆነ ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ተወያይቶ መክሮ ዘክሮ ድምጽ ሰጥቶ ሊቀይረው ይችላል። የፖለቲካ ድርጅቶቹ በምርጫ ተወዳዳሪ መሆንና ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለህዝባቸው መግለጽ እንደሚችሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ''ከውጭ እየገቡ ያሉት የፖለቲካ ሃይሎች አርማቸውን ሀሳባቸውን ፍልስፍናቸውን በሰላማዊ መንገድ ለህዝባቸው መንገር ማሳመን ይችላሉ ይሄው ምርጫ እየመጣ ነው  ከፊታችን ይበጀኛል ያዋጣኛል ካለ ይመርጣቸዋል። ሰው ሳይገሉ መኪና ሳያፈርሱ መንግስት መሆን ይቻላል። ለምንድነው እየዋልን እያደርን ወደ ኋላ የምንመለሰው ያልን እንደሆነ አልተለወጥንም።'' ''ገዥነት ያንገበገበን ሰዎች ረጋ ብለን በሀሳብ የምናሸንፍና በሰላም የምናገለግል እንድንሆን ልቦና ይስጠን'' ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም