1443ኛው ዒድ አል-አድሐ /ዐረፋ/ በዓል ሕዝበ ሙስሊሙ አብሮነቱን የሚያሳይበት ሊሆን ይገባል

92

ሀምሌ 1/2014/1443ኛው ዓመተ-ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ /ዐረፋ/ በዓል ሕዝበ ሙስሊሙ አብሮነቱን የሚያሳይበት ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት 1443ኛው ዓመተ-ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ /ዐረፋ በዓልን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ሱልጣን አማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓሉ በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የእምነቱ ተከታዮች ወደ ሳዑዲ በመጓዝ የሚያከብሩት ትልቅ በዓል መሆኑንም ገልጸው፤ አማኞች ወደ ፈጣሪያቸው በአንድነት ጸሎት የሚያደርጉበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር አቅመ ደካሞችን በመደገፍ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በዓሉ የሚከበረው በመተጋገዝ በአብሮነት እና በአንድነት እንደመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች አብሮነታችንን የምናሳይበት ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሸኽ አሊ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ በዓሉ በነገው እለት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ 2፡30 እንደሚከበር ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም በእድሳት ላይ በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ ስታዲየሙ አጠገብ ባለው የስፖርት መለማመጃ ቦታ ላይ የሶላት ስግደት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በዓሉ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ፣ በመርዳት እንዲሁም በጸሎት ሊከበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ በተለያዩ የልማት ሥራዎች በአረንጓዴ አሻራ ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የታላቁ አንዋር መስጂድ ኢማም ሀጂ ጣሀ መሀመድ፤ የዒዱ ቦታ በትንሹ ስታዲየም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

ሁሉም ሕዝበ ሙስሊም በዓሉን ሲያከብር በሰላም መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዓሉ ሲከበር አቅመ ደካሞችን በማገዝ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም