ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ አረፋ በአልን የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊያከበር ይገባል--ሼህ ሰይድ ሙሀመድ

77

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 1/2014 ( (ኢዜአ)፡ ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ አረፋ በአልን ሲያከብር የተቸገሩና የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ ሙሀመድ በነገው ዕለት የሚከበረውን የነቢዩ ሙሀመድ 1ሺህ 443ኛ የኢድ አል አድሃ አረፋ በአልን አስመልክተው ለእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ሲያከብር የተቸገሩና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብና በመረዳት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በታጠቁ ኃይሎች በንጹሀን ላይ  የተፈጸመው ጭፍጨፋ ልብን የሚሰብር ነው።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ንጹህን ዜጎች ሕይወታቸው በማለፉ ልባዊ ሀዘን እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ሁሌም ሰላምን ምርጫው በማድረግ የጥፋት አካላትን ተግባር ማክሸፍ እንዳለበት የመከሩት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግስት በንጹሐን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ቀድሞ መከላከል ላይ  እንዲሰራም ጠይቀዋል።

 ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ ሰላሙንና አንድነቱን ለማስቀጠል በትብብር መስራት እንዳለበት አመልክተው፤ "የቀደመ የአብሮነትና የመረዳዳት ባህላችንን በማጠናከር ሰላምን ማጽናት ከሁላችንም ይጠበቃል" ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ አረፋ በአልን ከተቸገሩ ወገኖችና ከሌሎች የእምነቱ ተከታይ ወገኖች ጋር አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር እንዳለበትም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም