በድሬደዋ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ፖሊስ መዘጋጀቱን አስታወቀ

123

ድሬዳዋ/ኢዜአ/ ሐምሌ 1/2014 (ኢዜአ) ነገ የሚከበረው የኢድ-አልደሃ /አረፋ/ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ፖሊስ መዘጋጀቱን የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ዲቪዢን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም  ግርማ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፖሊስ በዓሉ ያለምንም የፀጥታና የትራፊክ ችግር እንዲከበር ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ ተሰማርቷል፡፡

በተለይ በየቀበሌው ከሚገኙ የህብረተሰብ የፀጥታ አደረጃጀቶችና ወጣቶች ጋር በመቀናጀት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የተቀናጀ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

በገበያ አካባቢ ሊፈጠር የሚችል የስርቆት ተግባርን የመከላከል፣ ህብረተሰቡና አሽከርካሪዎች ከትራፊክ አደጋ ራሳቸውን መከላከል የሚችሉባቸውን ግንዛቤዎች በመፍጠር ላይ መሆናቸው ነው  ምክትል ኢንስፔክተሩ ያስታወቁት፡፡

በተለይ በበዓሉ ወቅት ህብረተሰቡ ተቀጣጣይ ቁሶችን በጥንቃቄ በመጠቀም ድንገት ሊፈጠር ከሚችል አደጋዎች ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲጋጥመው በስልክ ቁጥሮች በ0251111600 እና በ02511152 11 ለፖሊስ በማሳወቅ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም