በሚቀጥሉት 10 ቀናት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዝናብ ይጠበቃል

95
አዲስ አበባ መስከረም 3/2011 በሚቀጥሉት 10 ቀናት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዝናብ የሚጠበቅ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። በዝናቡ አማካኝነት የሚጠበቀው እርጥበት ለሰብሎች ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ከመሆኑም በላይ የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትንም ያጎለብተዋል። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጪዎቹ ቀናት የምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር አንደዚሁም ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉ አባ ቦራ፣ ምዕራብና ሰሜን ሸዋ ዝናብ ያገኛሉ ብሏል። የቤንሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች እንደዚሁም የምዕራብና መካከለኛው ትግራይ ዞኖች በመጪዎቹ አስር ቀናት ዝናብ ይኖራቸዋል። ከደቡብ ክልል የሀዲያ፣ ጉራጌ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ ጎፋ፣ የከፋና ቤንቺ ማጂና ሲዳማ፣ ጌዲዮ ዞኖች በአብዛኛው መደበኛና በጥቂት ቦታዎች ደግሞ ከመደበኛ በላይ ስርጭት ያለው ዝናብ የሚጠበቅባቸው ናቸው። የደቡብና የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎችም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከሚመጣው የደመና ሽፋን ጋር ተያይዞ የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ። መጪው ወቅት የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ሰብሎች ወደ ተሟላ ዕድገት የሚሸጋገሩበት በመሆኑ በዝናቡ አማካኝነት የሚጠበቀው እርጥበት ለሰብሎች ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋፅፆ አለው ተብሏልየግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማጎልበት ያለው ፋይዳም የጎላ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል። በምዕራብ አጋማሽና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ለሚገኙ የተለያዩ ሰብሎችና ቋሚ ተክሎች የተሟላ እድገት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም