በጋምቤላ ክልል የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሰራ እየተከናወነ ነው

121

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 1/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በክረምቱ ወራት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሰራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት አስታወቀ።

በክልሉ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል በበኩሉ፤ ከአጎራባች አካባቢዎች  በሚጥለው ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ጋር ተያይዞ  የጋምቤላ ክልልን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞች የጎርፍ አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ  ጠቁሟል።

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ዋና ዳሬክተር አቶ ጋድቤል ሙን ለኢዜአ እንተናገሩት፤ የሚቲዎሮሎጂ የአየር ትንበያን መሰረት በማድረግ የቅድም ጥንቃቄ ስራ እያከናወነ ነው።

የጥንቃቄው ስራ የክልሉ አብዛኛው ህዝብ አሰፋፈር ወንዞችን የተከተለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባሮ ፣የጊሎ፣ የአኮቦና የአሌሮ ወንዞች በሚኖረው ከባድ ዝናብ ሞልተው በመፍሰስ በነዋሪቹ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብር ኃይል ከክልል እስከ ወረዳ በማቋቋምና የጋራ እቅድ በመንደፍ የጎርፍ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ያለው ህዝብ   ወደ ደረቃማ ቦታዎች እንዲሰፍር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሚቲዎሮሎጂ ትንበያን መሰረት በማድረግ በተካሄደ ዳሰሳ ጥናትም አራቱ ታላላቅ ወንዞች በሚያልፍባቸው የኑዌርና የአኝዋሃ ዞን ስምንት ወረዳዎች  ነዋሪዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ስጋት መኖሩን ጠቁመዋል።

ስጋቱንም መሰረት በማድረግም መስሪያ ቤታቸው ከግብር ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የቅድመ አደጋ ምላሽ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደተገባም አስረድተዋል።

በዘንድሮው ዓመት ባሮን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ታላላቅ ወንዞች ከወትሮው በተለየ መልኩ ቀድመው መሙላታቸውን የጠቆሙት አቶ ጋድቤል፤ ከአሁን በፊትም የባሮ ወንዝ በተወሰነ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረስ አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ዓለሙ፤ የዘንድሮው ዓለም አቀፋዊ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ‘‘ላ ኒና ’’በመሆኑ የዝናቡ ስርጭት መጠን መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።

አሁን ላይ በጋምቤላ ክልል ሆነ በአጎራባች አካባቢዎች ያለው የክረምቱ ዝናብ ስርጭት  ወቅቱን የጠበቀ ቢሆንም ጊዜው የ‘‘ላ ኒና’’ ወቅት በመሆኑ የዝናብ ስርጭት መጠኑ እየተጠናከር እንደሚመጣ ገልጸዋል።

በዚህም ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎችና አካባቢ በሚጥለው ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ባሮን ጨምሮ ሌሎች ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ  የጎርፍ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በባሮ፣በጊሎና ሌሎች ታላላቅ ወንዞች አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊደረጉ እንደሚገባ ጠቁመው፤  ማዕከሉ ሊደርስ የሚችለውን የአደጋ መከላከል አደጋ ስጋት አገልግሎትና ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የመከካለኛውና ምስራቅ ፓስፊክ ውቅያኖስ ሙቀት መጠኑ ከመደበኛ በታች ሲሆን የ ‘‘ላ ኒና’’ ክስተት፤ የዚህ  ተቃራኔ ከሆነ ደግሞ ‘‘ኢሊኖ ’’ እንደሆነ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም