የህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር በህገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚፈጠር ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን መከላከል ይገባል

130

ሐምሌ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር በህገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚፈጠር ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን መከላከል እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲዎች ገለጹ፡፡

የአማራና የደቡብ ክልሎች የህብረት ስራ ኤጀንሲዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ህገ-ወጥ ደላሎች የግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት እያባበሱት ይገኛሉ፡፡

ከምርቱ ከፍተኛውን ገቢ ማግኘት ያለበት አርሶ አደሩ ቢሆንም በተቃራኒው ህገ-ወጥ ደላሎች ተጠቃሚ መሆናቸው ዘርፉን ይበልጥ እያዳከመው መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የደቡብ ክልል የህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አምሪያ ሲራጅ፤ ክልሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በብዛትና በጥራት ለማምረት ምቹ አካባቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዋናነት ቡና ፣ ሙዝ ፣ አፕልና የተለያዩ የግብርና ምርቶች በስፋት እንደሚመረቱ አብራርተዋል።

ምርቱን ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 30 የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዬኖች ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ 5 ሺህ 860 አርሶ አደሮች በህብረት ስራ ማህበራትና በዩኒዬን በአባልነት ቢታቀፉም ከሚያመርቱት ምርት አኳያ የሚያገኙት ጥቅም እምብዛም ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ህገ-ወጥ ደላሎች ገበያውን መቆጣጠራቸው አለፍ ሲልም የዋጋ ተመን እስከ ማውጣት የደረሰ ጣልቃ ገብነታቸው ተጠቃሽ ነው።

በመሆኑም የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማሳደግ እነዚህንና መሰል ችግሮች መከላከልና  የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።   

የአማራ ክልል የህብረት ስራ ኮሚሽን ኃላፊ ወልደትንሳኤ መኮንን በበኩላቸው በክልሉ የሚመረቱ ምርቶች ለገበያ ሲቀርቡ በህገ-ወጥ ደላሎች የተከበበ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የችግሩን አሳሳቢነትና የአርሶ አደሩን ተደጋጋሚ ቅሬታ ከግምት በማስገባት የቁጥጥርና የክትትል ስራውን በማጠናከር ለውጥ ማምጣት መቻሉን ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በ23 ሺህ 559 ህብረት ስራ ማህበራት ውስጥ ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዬን በላይ አርሶ አደሮች ቋሚ አባል ሆነው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ ከደላላ ጋር የሚያደርገው ውል በአብዛኛው በመቋረጡ በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥ ደላሎች ሳቢያ የሚፈጠር መዋከብን በማስቀረት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ላይ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም