ሕፃናት ተገቢውን የሕግ ከለላና ድጋፍ እንዲያገኙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

80

አዲስ አበባ  ሰኔ 30/2014 /ኢዜአ/ ለሕፃናት ተገቢውን የሕግ ከለላና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የአፍሪካ ሕጻናት ቀን በሰኔ ወር በአፍሪካ ለ32ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ ሲከበር ቆይቶ በዛሬው እለት በወዳጅነት አደባባይ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና መሐመድ፤ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ሕጻናት ላይ በርካታ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሕፃናት ተገቢውን የሕግ ከለላና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህጻናት መብትና ደህንነት ቻርተርን የአገሪቱ የህግ አካል አድርጋ እየሰራች ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ የአካል፣ የጤና እንዲሁም ህይወትታቸው ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በወንጀል የሚያስጠይቁ እንዲሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ መካተቱንም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀና የሺንጉስ፤ ማኅበረሰቡ ስለ ሕጻናት መብትና እንክብካቤ በበቂ ሁኔታ እንዲገነዘብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕጻናት ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን፣ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ በተለይም በትምህርት ቤቶች ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዘንድሮው የአፍሪካ ሕጻናት ቀን "ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በጋራ እንከላከል" በሚል መሪ  ሃሳብ ነው የተከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም