የነዳጅ ማደያዎች በቴሌ ብር አማካኝነት ብቻ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል-ቢሮው

520

ሐዋሳ፣ ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡበ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የክልሉ ነዳጅ ማደያዎች መንግሥት በዘረጋው ቴሌ ብር አማካኝነት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳሰበ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ አዋጅ ትግበራን በማስመልከት ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ክልሉ ውስጥ ካሉት 125 ነዳጅ ማደያዎች መካከል 13ቱ ስራ ላይ አይደሉም።

በስራ ላይ የሚገኙ ማደያዎች ከትናንት ጀምሮ መንግሥት በዘረጋው የነዳጅ ሪፎርም መሠረት ነዳጅ በድጎማ እና ያለ ድጎማ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ከቢሮው፣ ከመንገድ ትራንስፖርት፣ ከቴሌ ኮም እና ከፀጥታ አካላት የተውጣጣ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በየደረጃው እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ሆኖም አንዳንድ የማደያ ባለቤቶች ቴሌ ብር አላስመዘግብም፣ አልጠቀምም የማለት አዝማሚያ እያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ከቀጠሉ ተጎጂ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።

ሥርዓቱንና አሰራሩን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ሙከራ ቢሮው እንደማይታገስና የንግድ ፈቃድ ለመንጠቅ እንደሚገደድ አሳስበዋል።

በክልሉ የሚገኙ ማደያዎች በቴሌ ብር አገልግሎት መስጠን እንዳለባቸው ገልጸው፤ ተሽከርካሪዎችም ድጎማ የሚያገኙት በቴሌ ብር ብቻ መሆኑን ማወቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የታለመ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶችና ሹፌሮች የቴሌ ብር መተግበሪያ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስረድተዋል።

በቴሌ ብር መተግበሪያ ብቻ ክፍያ ስለሚፈጽሙ ቀድመው መመዝገብና የራሳቸውን ምስጢር ቁጥር በአግባቡ እንዲይዙ አሳስበዋል።

በመጀመሪያው ቀን ትግበራ ቴክኖሎጂው አዲስ በመሆኑ ያጋጠመ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታት የቴሌ ኤጀንቶች በሁሉም ማደያዎች ተመድበው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

መተግበሪያው ማጭበርበርን እንደሚያስቀር ገልጸው፤ ከዚህ በፊት ነዳጅ በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት በማጓጓዝ በግለሰብ ነጋዴዎች ሲመዘበር የቆየውን ሀብት አስቀርቷል ብለዋል።

ዋጋ ማሻሻያው ከጅምሩ መፍትሄ ይዞ መጥቷል ያሉት ኃላፊው፤ ወደ ፊትም ሀገራችን ላይ የነዳጅ ስርቆት ለማስቀረት ጠቃሚ ስትራቴጂ እንደሆነ ሁሉም በመገንዘብ ለተፈጻሚነቱ እንዲተጋ አቶ ማሄ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም