የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በመቋቋም ልማትን ማፋጠን ይገባል-ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

96

ሚዛን አማን፤ ሰኔ 30/2014 (ኢዜአ)፡ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በጋራ ተቋቁሙ በማለፍ ልማትን ማፋጠን እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩን አጠናክሮ በማስቀጠል ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ አካባቢን ለማውረስ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።

አራተኛው ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ዛሬ  ተጀምሯል።

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ229 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለመትከል መታቀዱ ነው የተገለጸው።

በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የውጭና የውስጥ ፈተና ተጋርጦባታል።  

 

ይህን የውስጥና የውጭ ፈተና በጋራ ተቋቁሞ ችግሩን ማለፍና በየደረጃው ልማትን ማፋጠን እንደሚገባም ተናግረዋል።

"የሀገርና የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ ቆርጠው በተነሱ የጥፋት ሃይሎች ሴራ እጅ ባለመስጠት አጥፊዎችን በጽናት ታግሎ ችግሩን በጋራ መሻገር ይገባል" ብለዋል።

እንደ ሀገር የሚካሄደውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አጠናክሮ በማስቀጠል ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ አካባቢን የማውረስ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ህዝብ ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህሉን በማጠናከር ለምግብነት፣ ለብዝሃ ሕይወትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚሆኑ ችግኞችን በመትከል ለቀጣዩ ትውልድ የለማች ሀገር እንዲያቆይም ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፣ በአራተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ229 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በክልሉ ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።

የሚተከሉ ችግኞች ለአካባቢ ጥበቃ ከሚኖራቸው ፋይዳ በተጨማሪ ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።  

ሕብረተሰቡ በክረምት ወቅት ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በጠሎ ወረዳ ሻዳ ቀበሌ ዛሬ በተካሄደው ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም