በኢትዮጵያ የባንኮች ሃብት 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ደርሷል

139

ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የባንኮች ሃብት 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ አስመልክተው ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በአገሪቱ ያሉት ባንኮች አጠቃላይ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ በአሁኑ ወቅት የባንኮች አጠቃላይ ሃብት 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ደርሷል ብለዋል።

በመላው አገሪቱ ከ8 ሺህ በላይ የባንኮች ቅርንጫፎች ያሉ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር 17 በመቶ አድጓል ብለዋል።

ባንኮቹ በዘንድሮው በጀት ዓመት 353 ቢሊዮን ብር ብድር ማቅረባቸውን አክለዋል።

በተመሳሳይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ በኤክስፖርት ምርት ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቧንም አንስተዋል።

ባለፉት አስር ዓመታት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመጨመር የወሰደውን ጊዜ ባለፉት ሁለት ዓመት ብቻ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱም የአገሪቱ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት የ10 በመቶ እድገት በማሳየት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የተከናወነው የለውጥ ስራ ውጤት ማሳየቱን ጠቅሰው ቡና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘበት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሻይ፣በአትክልት እና ፍራፍሬ ማስፋት ከተቻለ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም