የባህርዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማካሄድ እንዲችል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ

148

ባህርዳር፣ ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) ''የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ያስቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት በአጭር ጊዜ አሟልቶ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማካሄድ እንዲችል አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ይደረጋል'' ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገለፁ።

ከካቢኒያቸው ጋር የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን የጎበኙት ርዕሰ መስተዳድሩ በካፍ እንዲሟሉ የተጠየቁ ዝቅተኛ መስፈርቶች ተሟልተው የተቋረጠው ዓለም አቀፍና ክልል አቀፍ ውድድሮች እንዲጀመሩ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ትልቅ ሃብት ፈሶበት የተገነባው ስታዲየም በጥቃቅን ነገሮች አለመሟላት የከተማው ህዝብ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ ማድረጉን ገልጸው፤ ስታዲየሙን የተሟላ ለማድረግ 700 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅሰዋል።

''በስታዲየሙ የሚገኙ ሱቆች፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የእጅ፣ የመረብና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎችና ሌሎችም ደረጃቸውን ጠብቀው ለነዋሪው ህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል'' ሲሉ አስታውቀዋል።

እንዲሁም በወልዲያ ከተማ የተገነባው የሸህ ሙሀመድ አላሙዲን ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያደርግ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ዕገዛ እንደሚደረግም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው የባህርዳር ስታዲየም በ800 ሚሊዮን ብር ወጭ 98 በመቶ ግንባታውን በማጠናቀቅ ለውድድር ክፍት እንዲሆን ተደርጓል።

በዚህም ስታዲዮሙ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ሀገር አቀፍና አለም ዓቀፍ ውድድሮችን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው፤ ካፍ ስታዲየሙ እንዲያሟ ከጠየቃቸው ዝቅተኛ መስፈርቶች መካከልም የመቀመጫ ወንበር፣ የጣሪያ ልባስ፣ የተጨዋቾች የመልበሻ ክፍሎችና መቀመጫዎች፣ የመጫዎቻ ሜዳ ሳር ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ጥያቄ አቅርቧል ብለዋል።

እንግዶች ውድድሮችን የሚመለከቱበት ደረጃውን የጠበቀ መቀመጫ ቦታዎችና የተጫዋቾ ሻዎር ክፍሎች ካፍ እንዲሟሉ ከጠየቃቸው ዝቅተኛ መስፈርቶች መካከል እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።

እነዚህን ጥያቄዎች በወቅቱ ማሟላት ባለመቻሉም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስታዲየሙ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ መታገዱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስትም ችግሩን ተመልክቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠየቀውን ዝቅተኛ መስፈርት አሟልቶ በቀጣይ ውድድር እንዲካሄድበት በጀት መመደቡን ገልጸዋል።

በተመደበው በጀትም የተጠየቁ ዝቅተኛ መስፈርቶችን አሟልቶ ውድድሩን ለማስጀመር በትኩረት ቢሮው እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም