ኢትዮጵያ ወደ ዳገት ጉዞ ላይ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

170

ሰኔ 30/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ወደ ዳገት ጉዞ ላይ በመሆኗ በትብብር ደግፎ ወደ ከፍታ ማድረስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

የምክር ቤቱ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።

በምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ያጋጠሟትን ፈተናዎችና እየሄደችበት ያለውን መንገድ የተመለከተው ይጠቀሳል።።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኢትዮጵያ ወደ ዳገት ጉዞ ላይ መሆኗን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ወደ ዳገት ጉዞ ቅርብ ቢሆንም ልፋት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ወደ ኋላ መመለስ በአንጻሩ ሩቅ መሆኑን ጠቅሰው ጉዞው ግን የቁልቁለት በመሆኑ ቀላል ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን ደግፎ ወደ ላይ በመግፋት የከፍታውን ጉዞ ማሳካት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍላጎት ወደ ኋላ እንድንመለስ በመሆኑ የጠላትን ፍላጎት ከሚያሳኩ አካሄዶች መቆጠብ ይገባል ብለዋል።

ሀገር ወደ ዳገቱ የምታደርገውን ቅርብ ነገር ግን ከባድ መንገድ መደገፍ ያልቻለ አካል ደግሞ ቢያንስ ወደ ኋላ እንዳትመለስ ታኮ በማድረግ መሳተፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ይህም ካልተቻለ ግን ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚሰሩ ጠላቶች ተባባሪና መጠቀሚያ ላለመሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በባንዳነት ተሳትፎ አገርን ማፍረስ ትርፉ ጸጸትና መከራ መሆኑን ከየመንና ሊቢያ መማር ይገባል ብለዋል።

ችግሮችን ቻል አድርጎ በጋራ መሰለፍና ኢትዮጵያን ማጽናት እንደሚገባና የአገርን ጉዳይ ዋና አጀንዳ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም