በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሸሽገው አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አመራሮችን የማጥራትና እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል

77

ሰኔ 30/2014/ኢዜአ/ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሸሽገው አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አመራሮችን የማጥራትና እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስድስተኛ  ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ  ጉባኤውን  እያካሄደ ይገኛል።

የምክር ቤቱ አባላት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።

በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሸሽገው አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አመራርና ሰራተኞች በመኖራቸው በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ምን ይመስላል ሲሉ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐቢይ አህመድ፤ በምላሻቸው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሸሽገው አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አመራሮችን የማጥራትና እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

እነዚህ ሃይሎች የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የኢትዮጵያን ለውጥ ለማደናቀፍ ከአሸባሪዎችና ከባንዳዎች ጋር እየሰሩ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ጠላቶቻችን በመዋቅር ውስጥ ሰው እየገዙ መሆኑን ደርሰንበታል ይሄንን ለማጥራት እየሰራን ነው እስካሁንም በብዙዎች ላይ እርምጃ ወስደናል ብለዋል።

በመዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው በአገሪቱ ላይ እየተካሄደ ያለውን የተቀናጀ አሉታዊ የሚዲያ ዘመቻዎችን በማገዝና ዘመቻው የሚመሩ እንዳሉም ተናግረዋል።

እነዚህ ሃይሎች የኢትዮጵያን በጋራ የማኖርና የማጽናት ስራ እየጎዱት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥፋት ኃይሎች እስኪጠፉ ድረስ የጸጥታ ሃይሉ ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ የጸጥታ ኃይሎች ለአገር ህልውና እና ለህዝብ ሰላም ሲሉ ውድ ህይወታቸውን እየገበሩ ስለመሆኑን አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ህልውና እና ለህዝብ ሰላም ሲል  መንግስት የመከላከያ፣ የደህንነት እንዲሁም የፖሊስ መዋቅሩን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም