የተጣለብንን የገቢ ግብር በወቅቱ በመክፈል ሃላፊነታችንን ተወጥተናል- ግብር ከፋዮች

170

መተማ፤ ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን በመገንዘብ የተጣለባቸውን የገቢ ግብር ክፍያ በወቅቱ በመፈጸም ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብር ከፋዮች ገለጹ።

በበጀት አመቱ በዞኑ   ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ለመሰብሰብ  የታቀደውን ግብር  99   በመቶማሳካት መቻሉን የገቢዎች መምሪያ አስታወቋል።

ወይዘሮ እናንየ ደሴ በገንዳ ውሃ ከተማ በአነስተኛ የንግድ ስራ የተሰማሩ ሲሆን፤ ”ግብርን በወቅቱ መክፈል እፎይታን የሚሰጥና ያለ ጭንቀት ስራህን እንድትስራ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የተጣለባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሃላፊነታቸው መወጣታቸውን ገልጸው፤  በአነስተኛ ሱቅ ንግዳቸው ከ10 ሺህ ብር በላይ ግብር በወቅቱ  ገቢ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በአካባቢው በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ በየነ አዳነ በበኩላቸው ፤ በእርሻ ልማታቸው ከሚያገኙት ገቢ የሚጠበቅባቸውን የግብር ክፍያ በወቅቱ መፈጸማቸውን  ገልጸዋል።

ከመሬት መጠቀሚያ ብቻ ከ15 ሺህ ብር የሚጠጋና ከምርት ገቢ ደግሞ 100 ሺህ ብር የሚጠጋ ግብር መክፈላቸውን ተናግረዋል።

''ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ነው'' ያሉት ባለሃብቱ፤ ወቅቱን በመጠበቅ ግብር መክፈላቸው እፎይታ እንደሚሰማቸው አብራርተዋል።

በዞኑ የገቢዎች መምሪያ የግብር አሰባሰብና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ብርሃኑ አንዳርጌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ የገቢ አሰባሰብ ችግር ይገጥማል የሚል እሳቤ ነበር።

ሆኖም በተቀናጀ አግባብ በተከናወነው ስራ በዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 312 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከ310 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

በዚህም የዕቅዱን 99  በመቶው  ማሳካት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ይህም ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ መልካም የሚባል አፈፃፀም መሆኑን አስረድተዋል።

ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥም 274 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ከመደበኛ ፤ ቀሪው  ደግሞ ከከተማ አገልግሎት መሆኑን አመላክተዋል።

አካባቢው የጸጥታ ችግር  የታየበት ቢሆንም የተገኘው የገቢ እድገት የግብር ከፋዩ ግንዛቤ መሻሻሉ፣ የተቋሙ ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት ያደረጉት አስተዋፅኦ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ  ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ63 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ጭማሬ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የዘመኑን መልካም ተሞክሮዎቹን በማስፋት ለቀጣይ ዓመት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብም በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ7 ሺህ 200 በላይ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች እንዳሉ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም